በትምህርት ቤቶች ኮሮናን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት መምህራን ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በትምህርት ቤቶች ኮሮናን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት መምህራን ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የኮቪድ 19 ተፅዕኖን በመቋቋም ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለመክፈት የሚያስቸሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እየሰራ እንዳለ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ገልፀዋል፡፡
በዚህም የኮሮና ቫይረስን በመቋቋም ትምህርት ለመጀመር በሚደረግ ጥረት ውስጥ የመምህራን ድርሻ የጎላ መሆኑ አንስተዋል፡፡
ሚኒስትሩ እንደ ጤና ባለሙያዎች ሁሉ ኮሮናን በመቋቋም ትምህርት ለመጀመር በሚደረግ ጥረት መምህራንም ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም መምህራን በመማር ማስተማሩ ሂደት የሚኖሩ ጫናዎችን ተቋቁመው መደረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች በማድረግ የመማር ማስተማር ሂደቱን እንዲያከናውኑ ሚኒስትሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡