Fana: At a Speed of Life!

የኢሬቻ በዓል የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከል በሚያስችል መልኩ ተከብሯል-አቶ ሽመለስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  የኢሬቻ በዓል የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከል በሚያስችል መልኩ መከበሩ ትልቅ ስኬት መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመለስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የኢሬቻ በዓል መጠናቀቅን አስመልክቶ መገለጫ ሰጥተዋል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት የኢሬቻ በዓል በርካታ ሰዎች ተሳትፈውበት እንደተከበረ ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ዘንድሮ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ጥቂት ሰዎች ብቻ በተገኙበት ተከብሯል ብለዋል፡፡

በዚህም የበዓሉ ተሳታፊዎች የአባ ገዳዎችን መልዕክት በመስማት በጥንቃቄ ማክበር ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ይህም ታላላቆችን ማክበር አሁንም ያለ እሴት እንደሆነ አመላካች ነው ያሉ ሲሆን ይህም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

በአጠቃላይም በዓሉ በዚህ መልኩ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አባ ገዳዎች ፣ሲንቄዎች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የፀጥታ አካላት የአፍራሽ ኃይሎችን ምኞች በማክሸፍ ለሰሩት ስራ ምስጋና አቅርበዋል።

በሌላ በኩልም በዓሉ በአዲስ አበባ ሲከበር ነዋሪው እንግዶችን በመቀበል፣በዓሉ የሚከበርበትን ቦታ በማፅዳት እንዲሁም በመሳተፍ ላደረገው አስተዋፅዖ አመስግነዋል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የራሳችን እሴት አንዱ አካል ነው በማለት ተወካዮቻቸውን በመላክ በመሳተፋቸው አመስግነዋል፡፡

በመግለጫቸው እንዳሉት ይህ በዓል ለብዙ ዓመት እንዳይከበር መደረጉ እና ሲከበርም አፈና ይደረግ ነበር ብለዋል፡፡

ነገር ግን አባ ገዳዎች ይህን ሁሉ በመቋቋም እዚህ እንዲደርስ አድርገዋል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም የሚሉ አካላትን በተመለከተም ቀን በመቁጠር የሚፈርስ ሃገር የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ሐይሎች ከቀደመ ስህተታቸው ተምረው ወደ ትክከለኛው መንገድ ሊመለሱ ይገባል ነው ያሉት፡፡

እኔ የምለውን አስተሳሰብ አስወግደን እኛ በሚል አስተሳሰብ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ይህም እንዲሳካ ጠንክረን መስራት ይኖርብናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ማድረጋችንንም አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ከግብርና ስራዎች ጋር በተያያዘ በሰጡት አስተያየትም በክልሉ በግብርና እና በሌሎች ዘርፎች ሰፋፊ ስራዎች መሰራቱን ያነሱት ሲሆን እነዚህ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

በዜግነት አገልግሎትም በክልሉ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.