በአውሮፓ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተባባሰ በመምጣቱ እገዳዎች እየተጣሉ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአውሮፓ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ሃገራት የተለያዩ እገዳዎችን መጣል ጀምረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንትም በአንድ ቀን ብቻ 100 ሺህ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተነግሯል፡፡
ይህ ቁጥር ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ በአውሮፓ በአንድ ቀን የተመዘገበ ትልቁ ቁጥር ነው ተብሏል፡፡
ወረርሽኙ እየተባባሰባቸው ከሚገኙ ሃገራት መካከል ቼክ ሪፐብሊክ ዋናዋ መሆኗ ተነግሯል፡፡
እንዲሁም በፈረንሳይ እና በሩሲያ በየዕለቱ በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ እያለ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
በአውሮፓ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከ42 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡባት ብሪታንያ አዳዲስ ክልከላዎችን ለመጣል እየተዘጋጀች መሆኑ ተሰምቷል፡፡
በተጨማሪም የጣልያን የጤና ሚኒስቴር ክልከላዎችን ለማውጣት እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጿል፡፡
ምንጭ፥ ኤን ቢ ሲ ኒውስ