አውስትራሊያ፤ አሜሪካ፣ ጃፓን እና ህንድ የሚያደርጉትን ወታደራዊ ልምምድ ተቀላቀለች
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አውስትራሊያ ቻይና በልዩ ትኩረት የምትከታተለውን እና አሜሪካ፣ ጃፓን እና ህንድ በቤንጋል የባህር ዳርቻ የሚያካሂዱትን ወታደራዊ ልምምድ ተቀላቀለች።
አውስትራሊያ ከፈረንጆቹ 2017 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የምትቀላቀለው እና ሀገራቱ ህዳር ወር ላይ የሚያካሂዱት የማልባር የባህር ላይ ወታደራዊ ልምምድ በቻይና በኩል በበጎ አይን እንደማይታይ እየተነገረ ነው።
የአውስትራሊያ መከላከያ ሚኒስትር ሊንዳ ሬይንኖልድስ በቀጣዩ ህዳር ወር የሚደረገው ወታደራዊ ልምምድ፥ ለበለፀገ እና ክፍት ለሆነ ኢንዶ -ፓሲፊክ አካባቢ የተደራጀ መፍትሄ የሚቀርብበት ወታደራዊ ልምምድ ነው ብለዋል።
ይህ የሀገራቱ ልምምድ በአካባቢው ተፅዕኖዋን እያሳረፈች ለምትገኘው ቻይና አፀፋ ለመስጠት ያለመ መሆኑም ይነገራል።
የህንድ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ልምምዱ ቻይና እና ህንድ ስትራቴጂካዊ ፉክክር እያደረጉበት በሚገኘው የዓረቢያን ባህር እና የቤንጋል የባህር ወሽመጥ አካባቢ የሚከናወን መሆኑን አስታውቋል።
ቻይና ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት በማይናማር፣ ሲሪ ላንካ ፣ ፓኪስታን እና ባንግላዲሽ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር መሞከሯ በህንድ ላይ ስጋት ማጫሩን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ይህ ወታደራዊ ልምምድ በቻይና እና አውስትራሊያ ዲፕሎማቲክ፣ በአሜሪካ እና ቻይና መካከል ደግሞ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም በቻይና እና ህንድ መካከል ወታደራዊ ውጥረት በተፈጠረበት ወቅት የሚደረግ ነው ተብሏል።
ምንጭ÷ አልጀዚራ