የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባህሪያት ከሥርዓተ ምግብ ጋር ያለውን መስተጋብር የተመለከተ ጥናት ተጀመረ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 11 ፣2013 (ኤፍ.ቢ. ሲ) የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የኮቪድ19 ወረርሽኝ ባህሪያት ከሥርዓተ ምግብ ጋር ያለውን መስተጋብር አስመልክቶ ለአንድ አመት የሚቆይ ጥናት በይፋ አስጀመረ።
በዚህም በህክምና ማገገሚያ ውስጥ ቆይታ በነበራቸው ታካሚዎች ላይ ክትትል እና ጥናት በማድረግ መፍትሄዎችን ለማስቀመጥ የሚያስችል ለአንድ አመት የሚቆይ ጥናት በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት፣ ከጤና ሚኒስቴር እና ከልዩ ልዩ የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ለማከናወን ታቅዶ ሥራው በይፋ ተጀምሯል።
ለዚህ ጥናት ቢያንስ 100 ሚሊየን ብር ያስፈልገዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ÷ ጥናቱ በሃገሪቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዙሪያ የመከላከል፣ የምላሽ እና የምርመራ ሂደቶችን አጣምሮ የሚያስኬድ እና ስለቫይረሱ ተጨማሪ መረጃዎችን የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
የሚሰበሰቡ እና የሚገኙ መረጃዎችን ወደ ተግባር መለወጥ እንዲቻልም በጥናቱ ዙሪያ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
መሪ ተመራማሪ ወይዘሮ ሳሮ አብደላህ በበኩላቸው÷ ጥናቱ የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል አቅምን ለማሳደግ ከመስራቱም ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራ እና በርካቶችን የሚያሳትፍ ነው ብለዋል።
የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ የሃገሪቱን የመከላከል አቅምን ለማሳደግ የሚረዱ የምርምር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዙሪያ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በርካታ ጥናቶች እየተከናወኑ ቢሆንም ለጥናቶቹ ከግብ መድረስ ግን የበጀት እጥረት ፈተና መሆኑ ተነስቷል።
በጥናቱ ከ20 በላይ ከፍተኛ የትምህርት እና የምርምር ተቋማት እንዲሁም በሃገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ምሁራን ተሳታፊ መሆናቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።