Fana: At a Speed of Life!

በግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር የአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ሚና ከፍ ይበል በሚለው ሃሳብ ግብጽ ሳትስማማ መቅረቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕዳሴ ግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር ዙሪያ የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ሚና ከፍ ይበል በሚለው የኢትዮጵያ ሐሳብ ሱዳን ስትስማማ ግብጽ ሳትቀበል መቅረቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ባለፉት ሶስት ሳምንታት በዲፕሎማሲው መስክ የተሰሩት ስራዎችን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደሩ በመግለጫቸው ኢትዮጵያ፣ ሱዳን ፣ እና ግብፅ መካከል ላለፉት ሰባት ቀናት በህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ዙሪያ ምክክር እንዳደረጉ ገልፀዋል።

በምክክሩ ሶስቱም ሀገራት የድርድሩን ሞዳሊቲ ለማዘጋጀት እየንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ባለሙያዎች መርጠው እንዳቀረቡ አስታውቀዋል።

በድርድሩ ዙሪያ የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ሚና ከፍ ይበል በሚለው የኢትዮጵያ ሐሳብ ሱዳን ስትስማማ ግብጽ ሳትቀበል ቀርታለች ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፡፡

ሶስቱ ሀገራት የተስማሙባቸው እና ያልተስማሙባቸው ነጥቦችን ለወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና ለደቡብ አፍሪካ ሪፖርት ማድረጋቸውን አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳይ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ እያደረገች የሚገኘውን ድርድር እና ውይይት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተውን አቋሟን አንደማይቀይረውም ነው የተናገሩት፡፡

ወደ ፊትም ቢሆን ኢትዮጵያ የግድቡ ጉዳይ በአፍሪካ ህብረት እንዲፈታ የጀመረችውን ጉዞ አጠናክራ እንደምትቀጥል አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

በመግለጫው በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ኢትዮጵያ በልማቱ መስክ እየሰራቻቸው ከሚገኙ ስራዎች ልምድ መቅሰማቸውን እና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር አጥጋቢ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ እና የንግድ ሚኒስትር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት አግባብ ላይ ከመወያየታቸው በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለጅቡቲ ከታዳሽ ሀይል የምታቀርበው የሃይል አቅርቦት ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ዙሪያም መክረዋል ነው ያሉት።

ቃል አቀባዩ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በህወሓት መዋቅር ውስጥ የሚገኝ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ የፌደራል መንግስት ተገዶ የገባበትን ጦርነት በተመለከተ በአዲስ አበባ ለሚገኙ አምባሳደሮች እና የዲፕሎማቲክ አባላት ማብራሪያ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

ዲፕሎማቶቹ እና አምባሳደሮቹ የኢትዮጵያን ሰላም እንደሚፈልጉ እና ጉዳዩ በቶሎ እልባት እንዲያገኝ ፍላጎታቸው መሆኑም ነው የገለጹት።

ከዚህ ባለፈ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ጅቡቲ የኢትዮጵያ ሰላም የእነሱ ሰላም መሆኑን በመግለፅ ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆሙ ማስታወቃቸውን አምሳደሩ አንስተዋል።

በጥበበስላሴ ጀንበሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.