Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለባንግላዴሽ ፕሬዚዳንት አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለባንግላዴሽ ፕሬዚዳንት አብዱል ሀሚድ አቀረቡ።

ተቀማጭነታቸውን በኒው ዴልሂ ሆኖ የባንግላዴሽ ሪፐብሊክን የሚሸፍኑት የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ በትናንትናው እለት ነው የሹመት ደብዳቤያቸውን ያቀረቡት።

በዚሁ ወቅትም አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ ከባንግላዴሽ ፕሬዚዳንት አብዱል ሀሚድ የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ዙሪያ መወያየታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ በተለይም የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ህግን ለማስከበር እየወሰደ ያለውን እርምጃ አስመልክቶ ነው የተወያዩት።

የባንግላዴሽ ፕሬዚዳንት አብዱል ሀሚድ በአምባሳደር ትዝታ አማካኝነት ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰላምታ ልከዋል።

በተያያዘ ዜና አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ በባንግላዴሽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ክንፍ ዳይሬክተር ጀነራል ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና በባንግላዴሽ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት እና የሀገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት ከፍ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መክረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.