የአምባሳደር ስዩም ባለቤትና ልጃቸው ለህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የህክምናና የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር አለ መርማሪ ፖሊስ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአምባሳደር ስዩም መስፍን የትዳር አጋር ፈለገ ህይወት በርሄ እና ልጃቸው አጋዚ ስዩም ለህወሓት ከፍተኛ አመራሮች በድብቅ ህክምና እንዲያገኙ በማድረግ እና በገንዘብ ሲደግፏቸው እንደነበር መርማሪ ፖሊስ ገለጸ፡፡
ይህንን ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ሲሆን ተጠርጣሪዎቹ ዛሬ ለሦስተኛ ጊዜ ችሎት ቀርበዋል፡፡
መርማሪ ፖሊስ በዛሬው ችሎት በተሰጠው ጊዜ ውስጥም በርካታ ማስረጃ መሰብሰቡን ገልጾ ተጨማሪ ምስክር ለመቀበል ለብሄራዊ ደህንነት የላከውን ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ምርመራ ለመቀበል እና ሌሎች ምርመራዎችን ለማከናወን ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጿል፡፡
እንዲሁም ባካሄድኩት ምርመራ ለከፍተኛ አመራሮች የህክምና ድጋፍ ሲያደርጉና መድሐኒት እየገዙ ይልኩ እንደነበር እና የህክምና ድጋፍ ሲያደርጉላቸው እንደነበር በማስረጃ ማረጋገጡን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ ተሳትፏቸውን ሲገልጽ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በገንዘብ በማመቻቸትም ሲረዱ ነበር ብሏል ለችሎቱ፡፡
በችሎቱ ውስጥ ከጠበቃቸው ጋር የተገኙ ተጠርጣሪዎቹ ተጨማሪ ምስክር ለማስመረጥ መባሉ አግባብነት የለውም የዋስትና መብታቸውን ለማስከልከል ነው ሲል ጠበቃቸው ተቃውሟል፡፡
ጠበቃቸው ለኢንሳ የተላከው የኤለሌክትሮኒክስ ምርመራም ቢሆን ከነሱ ጋር አይገናኝም አድራሻ ስላላቸው ዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቋል፡፡
መርማሪ ፖሊስም በጠበቃው የቀረበውን የዋስትና መብት ይሰጣቸው የሚለውን ጥያቄ ተቃውሟል፡፡
መርማሪ ፖሊስ ኤሌክትሮኒክስ ምረመራው የተለዋወጡዋቸው የድምጽና የጽሑፍ መልዕክቶችን ለማስመርመር መሆኑን ገልጿል፡፡
እንዲሁም ተጠርጣሪዎቹም አድራሻቸውን እንዲያስመዘግቡ በተጠየቁበት ወቅት በቂ አድራሻ እንደሌላቸው መግለጻቸውን አስታውሷል፡፡
በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ምስክር ሊያባብሉ ይችላሉ በማለት ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡
የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሁለተኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎትም መርማሪ ፖሊስ ቀረኝ ላላቸው የምርመራ ስራዎች ስምንት ተጨማሪ ቀናትን ፈቅዷል፡፡
በታሪክ አዱኛ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!