በኢትዮጵያ ላፕቶፕና ታብሌት ለማምረት የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የላፕቶፕ እና ታብሌት ምርት መጀመር የሚያስችላትን ሥራ እያከናወነች ነው አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በአንድ መድረክ የሚያጣምረውን የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ÷ የዳታ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በየተቋማቱ ተግባራዊ ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንንም ይበልጥ ለማጠናከርና ኢትዮጵያ ወደ ሃርድዌር ምርት መሸጋገር እንዳለባት በማመን የኤአይ ኢንስቲትዩት ከሌላ ተቋም እና ከኤአይ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የላፕቶፕ እና የአይፓድ ፋብሪካ ግንባታ ላይ በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ይህ በሶፍትዌርና ዳታ ላይ የታየው ብቃት ወደ ሃርድዌር ምርት ሲያድግ ለቀጣዩ ትውልድ ሙሉ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት መፍጠር የሚያስችል መሰረት እንደሚጥል አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት የቴሌብር ተጠቃሚዎች ቁጥር 55 ሚሊየን መድረሱን አንስተው ÷ ይህም ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው መስክ እያመጣች ያለውን ለውጥ ማሳያ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ የተሰጣቸው ዜጎች ቁጥር 45 ሚሊየን ላይ መድረሱን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመላከቱት፡፡
በቨርቿል ሰርቪስ፣ በቢፒኦ እና በስታርትአፕ ለመቀጠር የሚያስችል መሰረት ያላቸው 5 ሚሊየን ኮደሮች በሀገር ውስጥ መሰልጠን መቻላቸውም ሌላኛው ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ቁጥር በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች 70 መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡
ከስድስትና ሰባት ዓመታት በፊት ከጄነራል መኮንኖች ጋር ስለ ድሮን ቴክኖሎጂ ማውራት እንደ ቅዠት ይታይ እንደነበር አስታውሰው ÷ በአሁኑ ወቅት ግን የሕግ አስከባሪ ተቋማት ብቃታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጋቸውንና ኢትዮጵያም ድሮኖችን በስፋት ማምረት መጀመሯን አስገንዝበዋል።
የምንመኘውን ብልጽግና፣ ሉዓላዊነት እና የጸና ሀገር ግንባታ ለማረጋገጥ ቴክኖሎጂ በእጅጉ የሚያግዝ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ጉዳዩን ከልቡ ወስዶ ሊሰራበት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በሶስና አለማየሁ