በጋምቤላ ክልል ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውር የተገኘ ግለሰብ በቀጥጥር ስር ዋለ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 12 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውር የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ኮማንደር ኡማን ኡጋላ ÷ ግለሰቡ በቀጥጥር ስር የዋለው ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠረፍ ከሚገኘው ዋንተዋር ወረዳ አቋርጦ ወደ ኢታንግ ልዩ ወረዳ ጦር መሳሪያዎችን በሸክም ለማስገባት ሲሞክር ነው ብለዋል።
የጦር መሳሪያዎቹ አምስት ታጣፊና ሁለት ባለሰደፍ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ተጨማሪ የማጣራት ሥራው እንደተጠናቀቀም ጉዳዩ ለፍርድ ቤት እንደሚላክ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር ባደረገው ጥረት 352 የክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች እና ከ1 ሺህ 870 በላይ ተተኳሽ ጥይቶች መያዙን ኮማንደር ኡማን አስታውሰዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በጦር መሳሪያ አዘዋዋሪነት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት 12 ግለሰቦች መካከል በአምስቱ ላይ ከስምንት እስከ አስር ዓመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት እንደተወሰነባቸውና የቀሪዎቹ ጉዳይም በፍርድ ቤት በሂደት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም የጦር መሳሪያ ዝውውሩን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ህዝቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚሽነሩ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!