የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክን ከአደጋ ለመታደግ የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክን ከአደጋ ለመታደግ እና በዘላቂነት ለማስጠበቅ ያለመ የባለድርሻ አካላት የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ።
በፓርኩ ክልል ለሰፈሩ ሰዎች አማራጭ ቦታ የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት ገልጿል፡፡
በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደው የባለድርሻ አካላት የመግባባያ ሰነድ መፈራረሚያ ስነ -ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
በተለይም በፓርኩ ውስጥ የሚካሄደው ህገ-ወጥ ሰፈራ እና ልቅ ግጦሽ ለችግሩ መባባስ በዋናነት የሚጠቀስ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አባያ እና ጫሞ ሐይቆችም በደለል የመሞላት አደጋ የተጋረጣባቸው ሲሆን በህገ- ወጥ መንገድ የሚካሄደው የዓሳ ማስገር ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የመግባባያ ሰነዱ ዋና ዓላማ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በመስራት ለፓርኩ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት እና በአዋሳኝ የሚኖሩ ህዝቦችን የኑሮ ሁኔታ ለመለወጥ ያለመ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የቀድሞ ጠቅላይ ሚስቴር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክን ከአደጋ ለመታደግ እና በዘላቂነት ለማስጠበቅ ባለድርሻ አካላት እና አመራሩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ እንደገለፁት የክልሉ መንግስት በፓርኩ ክልል ለሰፈሩ ሰዎች አማራጭ ቦታ የመለየት ስራ እያከናወነ ነው ፡፡
የፓርኩን አዋሳኝ ቦታዎች ከማስጠበቅ ጎን ለጎንም የአካባቢውን ህብረተሰብ ህይወት ለመለወጥ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ፓርኩን እንደመደበቂያ በሚጠቀሙ ህገ-ወጥ አካላት ላይም ሕግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አቶ አዲሱ ገልፀዋል፡፡
በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እንዲሁም የእርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ የክልሉ መንግስት የመግባቢያ ሰነዱ ተፈፃሚ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደረግ ጠቁመው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለወሰደው ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የጋሞ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ዙሪያ ተደጋጋሚ ውይይቶች ቢካሄዱም መፍትሔ ሳያመጡ መቆታቸውን አስታውሰው የመግባቢያ ሰነዱ ተፈፃሚ እንዲሆን በቁርጠኝነት መስራት ከባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክን ከአደጋ ለመታደግ እና በዘላቂነት ለማስጠበቅ ዓላማ ባደረገ የመግባቢያ ሰነድ ላይ 48 ባለድርሻ አካለት ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!