ለባህል መድሃኒት አዋቂዎች መሰረታዊ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ላይ ስልጠና እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከኢትዮጵያ ከሁሉም ክልልሎች ለተውጣጡ ለባህል መድሃኒት አዋቂዎች መሰረታዊ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ላይ ስልጠና መስጠት መጀመሩን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ የባህላዊ እና ዘመናዊ መድሃኒት ምርምር ዳይሬክቶሬት ወይዘሮ ፍሬህይወት ተካ ስልጠናው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 30 በአዳማ ከተማ ሁለተኛው ዙር ስልጠና መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
የስልጠናው ዋና አላማ በኢትዮጵያ የጤና አጠባበቅ ስርዓት፣ፖሊሲዎች፣ደንቦች፣ መመሪያዎች እንዲሁም የህክምና ስነ-ምግባር እና የሰዎች መብት ላይ ለባህል መድሃኒት አዋቂዎች ስልጠና በመስጠት የባህል ህክምናን ከብሄራዊ የጤና ስርዓት ጋር በቅንጅት እንዲሰራ በማድረግ ዘርፉ እንዲሻሻልና የባህል መድሃኒት አዋቂዎች በጤና ስርዓቱ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ነው ተብሏል፡፡
ወይዘሮ ፍሬህይወት ተካ በስልጠናው የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት እንደገለጹት 80 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ ህዝብ የባህል መድሀኒት ተጠቃሚ እንደሆነ ገልጸው ናይጄሪያና ጋና የባህል መድሃኒትን ከዘመናዊ መድሃኒት ጋር አቀናጅተው በመጠቀም ባህል መድሃኒትን ከፍተኛ ደረጃ ማድረሳቸውን አንስተዋል፡፡
እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ህንድ እና ቻይና የባህል መድሃኒትን ለገበያ በማብቃት ታላቅ ስራ መስራታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ዳይሬክቶሯ በኢትዮጵያ ለ40 ዓመታት ከባህል መድሃኒት አዋቂዎች ጋር በርካታ ስራዎች ኢንስቲትዩቱ መስራቱን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት መንግስት ከሌላው ጊዜ በተሻለ መንገድ ለባህል መድሃኒት ትኩረት በመስጠቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለባህል መድሃኒት አዋቂዎች የተለያዩ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት፡፡
ኢንስቲትዩቱ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ላይ የባህል ህክምና በሚኖረው ድርሻ መሰረት የበኩሉን አስትዋጽኦ እንዲያበረክት ለማድረግ ሁለተኛው ዙር ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ መናገራቸው ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የባህል መድሃኒት በኢትዮጵያ፣ የጤና አጠባበቅ ስርዓት፣የባህል መድሃኒት እውቀትና የአዕምሮአዊ ንብረት አያያዝ ምን እንደሚመስል፣የባህል መድሃኒት የአመዘጋገብ ሂደት፣ጤና እና ምግብ ያላቸው ግንኙነት፣መድሃኒትነት ያላቸውን እጽዋቶች መንከባከብ እና እንዴት መተካት እንደሚቻል እንዲሁም የህክምና ስነ-ምግባር ላይ ስልጠናው ትኩረት አድርጎ እየተሰጠ መሆኑን ከስልጠናው አስተባባሪዎች መረዳት ተችሏል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!