Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ሠብዓዊ ድጋፍ አግኝተዋል …ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ሠብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉን የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
በክልሉ 800 ሺህ ዜጎች የአልሚ ምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ​ብለዋል።
ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሊን የተመራ የልዑካን ቡድን በትግራይ ክልል በመንግስት እየተካሄደ ያለውን የሠብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥ ዛሬ ተመልክቷል።
የልዑካን ቡድኑ በመቀሌ የሚገኘውን በፌዴራል መንግስት ማዕከላዊ መጋዘን ለሰብዓዊ ድጋፍ የተዘጋጀ እህልና በመቀሌ አቅራቢያ ኩዊሃ አካባቢ የሚገኘውን የሰብዓዊ ድጋፍ ማዕከል ጎብኝቷል።
የሠላም ሚኒስትሯ መንግስት ባደረገው የመጀመሪያ ዙር የዳሰሳ ጥናት በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች መለየታቸውን ገልጸዋል።
የሠብዓዊ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ዜጎች እስካሁን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮኑ ድጋፍ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም በፍጥነት ድጋፍ ለሚሹ ሴቶችና ህጻናት አልሚ ምግብ እየተሰጠ ሲሆን ድጋፉ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር እየቀረበ ይገኛል ብለዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ ከውጭ አገር የተገዛ ስንዴ ትናንት ወደ መቀሌ ማዕከላዊ መጋዘን መግባቱንም ጠቁመዋል።
በመቀሌ ማዕከላዊ መጋዘን በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ ለሚያሻቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ለሁለት ወር የሚበቃ የምግብ ክምችት መኖሩንም ነው ወይዘሮ ሙፈሪያት የገለጹት።
አልሚ ምግብ ለሚሹ 800 ሺህ ወገኖችም ግዢ እየተከናወነ መሆኑንና የዛሬው ጉብኝት በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ግዢው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በተጨማሪም የሠብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
መንግስት በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች በተመለከተ የሁለተኛ ዙር የዳሰሳ ጥናት እንደሚያካሂድም አክለዋል።
የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሣ በበኩላቸው በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፉን በተፋጠነ ሁኔታ ለማድረስ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ተቋቁሞ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ማዕከሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተወጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ እንደሆነ ገልጸዋል።
በማስተባበሪያ ማዕከሉ አማካኝነት የሚመጣውን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ለዜጎች እየደረሱ መሆኑንም ገልፀዋል።
ጉብኝቱ አጋር አካላት በትግራይ ክልል የሚያደርጉትን ድጋፍ የሚያጠናክሩበትን ሁኔታ እንደሚፈጥርም ነው ኮሚሽነር ምትኩ የጠቆሙት።
በተያዘው ሳምንት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ ጋር በነበራቸው ውይይት በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች 80 በመቶውን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.