ስድስተኛው የናይል ተፋሰስ ልማት ፎረም ተጀመረ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚከናወነው ስድስተኛው የናይል ተፋሰስ ልማት ፎረም ዛሬ ተጀመረ፡፡
የፎረሙ ማስጀመሪያ መርሃግብር የተካሄደው ዛሬ ዑጋንዳ ባስተናገደችው በዌቢናር በተደረገው 22ኛው የናይል ቀን ሲከበር ነው፡፡
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የናይል ቀንን አስመልክተው በናይል ተፋሰስ ሃገራት ምስራቃዊ ክፍል ድንበር ተሻጋሪ የሆነ ኢንቨስትመንት ማድረግ በሚል ርዕስ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡
የናይል ተፋሰስ ሃገራት አካባቢያዊ ፣ታሪካዊና ባህላዊ የሆነ ጥብቅ ትስስር ያላቸው በመሆኑ የህዝብ ቁጥሩን ጨምሮ ያለውን ተፈጥሯዊ እምቅ አቅም ለመጠቀም በጋራ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ይገባል ብለዋል፡፡
ይህን ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ በትኩረት መመልከትና መስራት እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ወንዙን በአግባቡ ተጠቅሞ የአካባቢውን ነዋሪዎች መሰረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
የህዳሴ ግድብን በተመለከተም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት መሪነት እየተካሄደ ያለው ድርድር ውጤት ያስገኛል ብላ እንደምታምንም ተጠቁሟል፡፡
ፎረሙ በናይል ተፋሰስ አካባቢያዊ ኢንቨስትመንትን በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን፥ ውሃ፣ ኃይል፣ ምግብ፣ አካባቢና የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የ10 ዓመቱን የናይል ተፋሰስ ስትራቴጂን መሰረት በማድረግ ሃሳብ የሚቀርብበት ነው ተብሏል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!