ጠ/ሚ ዐቢይ በባህር ዳር ከተማ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን ድልድይ የግንባታ ሂደት ጎበኙ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በባህር ዳር ከተማ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን ድልድይ የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የፌደራልና የአማራ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የድልድዩ ግንባታ መጠናቀቅ ዘመናዊ እና አማራጭ የመጓጓዣ መንገድ እንዲኖር በማስቻል የወጪ ንግድ ቀጠና ውጤታማነትን ያቀላጥፋል ብለዋል።
የድልድዩ ግንባታ ሂደት 25 በመቶ መድረሱም በዚህ ወቅት ተገልጿል፡፡
ድልድዩ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅም ይሰራል ተብሏል፡፡
አዲሱ ድልድይ ነባሩንና በአገልግሎት ብዛት ለጉዳት የተዳረገውን ድልድይ የሚተካ ሲሆን፥ ግንባታው በቻይናው ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ እንዲሁም የቱርኩ ቦቴክ እና የሃገር ውስጥ አማካሪው እስታዲያ በተቆጣጣሪነት እና በአማካሪነት እያገለገሉ ነው፡፡
ድልድዩ 380 ሜትር ርዝመትና 43 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን፥ ከተሽከርካሪ በተጨማሪ የብስክሌት መስመር የእንግረኛ መንገዶችንም ያካተተ ነው ተብሏል፡፡
ባለፈው አመት የተጀመረው የድልድዩ ግንባታ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ አጠቃላይ ወጪውም በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው።
በአሁኑ ወቅት አራቱም የቋሚ ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ የሚያርፈው የመጀመሪያው የኮንክሪት ሙሌት ስራ ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ /የገርደር /ወይም የላይኛው የድልድዩ ክፍል የኮንክሪት ሙሌት ስራ ከሶስት ቀን በፊት መጀመሩ ይታወሳል፡፡
በዓላዛር ታደለ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!