Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ሬቤካ ኒያንዴንግ ዲማቢዮር ጋር በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ አምባሳደር ነቢል የሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ሁኔታ እንዲሁም የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታና በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ዙሪያ ለምክትል ፕሬዝዳንቷ ገለጻ አድርገዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለደቡብ ሱዳን ዘመን የማይሽረው ውለታ መዋላቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህም ደቡብ ሱዳን የሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስኗትን ሦስት ክልሎች ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ መኖሩን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ውዝግብም በውይይት መፍታት የሚገባው መሆኑን ገልጸው ደቡብ ሱዳን ችግሩ በውይይት እንዲፈታ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ከዚህ ባሻገር በትግራይ ያለው ሁኔታ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ተስተካክሎ በኢትዮጵያ ዘላቂ መረጋጋት እንደሚመጣ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ምርጫ ለማከናወን የሚያስችል ልምድና ተሞክሮ እንዳላት በማስታወስ ቀጣዩም አገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን እምነት መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በመጨረሻም የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት አፈጻጸም የዘገየ ቢሆንም በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆኑን አረጋግጠው ኢትዮጵያም ለሂደቱ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.