የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን ለቆ መውጣት ሃገሪቱን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንዳይከታት ተሰግቷል
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን ለቆ መውጣት በሃገሪቱ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል ሲሉ ከፍተኛ የአሜሪካ ወታደራዊ አዛዥ አስጠነቀቁ፡፡
በአፍጋኒስታን የአሜሪካ መራሹ ጦር አዛዥ ጀኔራል ስኮት ሚለር፥ የአሜሪካ ጦር ከሃገሪቱ እየለቀቀ መውጣቱን ተከትሎ “አፍጋኒስታን እጅግ አስቸጋሪ ጊዜን ልትጋፈጥ ትችላለች” ብለዋል፡፡
አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ወታደሮቿን ማስወጣት ከጀመረችበት ካለፈው ወር መጨረሻ ጀምሮም የታሊባን ታጣቂዎች በርካታ አካባቢዎችን መቆጣጠር መጀመራቸው ተሰምቷል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታና ደህንነት ስጋቶች እንዳሉና የእርስ በእርስ ጦርነትም በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
በሃገሪቱ ለሚስተዋለው የፀጥታና የደህንነት ስጋት ታሊባን ከአሜሪካ ጋር የደረሰውን ስምምነት አለማክበሩ እና ወደ ሽምቅ ውጊያ መመለሱ ምክንያት መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ፡፡
የታሊባን ታጣቂዎች አሁን ላይ 100 አካባቢዎችን እያስተዳድረን እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በአንጻሩ ከግንቦት ወር ጀምሮ ባለው ጊዜ ታጣቂዎቹ በሃገሪቱ ከሚገኙ 370 አስተዳደራዊ አካባቢዎች 50ዎቹን መቆጣጠራቸውን የሃገሪቱን ባለስልጣናት ዋቢ ያደረገው የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል፡፡
በርካታ አካባቢዎችን ከማስተዳደር ባለፈም መዲናዋ ካቡልን መክበባቸውም ነው እየተነገ ያለው፡፡
በሌላ በኩል የአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት አሽረፍ ጋኒ የሀገራቸው የፀጥታ አካላት በሙሉ አቅሙ የሰርጎ ገቦችን ጥቃት መመከት በሚችልበት ደረጃ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ጦር እስከ ፈረንጆቹ መስከረም 11 ቀን ድረስ አፍጋኒስታንን ሙሉ በሙሉ ለቆ እንደሚወጣ ይጠበቃል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ምንጭ፡ ቢቢሲ