የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን አገልግሎቱን ለማዘመን እየሰራ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርት አገልግሎቱ በቴክሎጂ በማስደገፍ ለማዘመንና ለማቀላጠፍ እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣኑ የ2013 በጀት ዓመተ የስራ አፈፃፀምና የቀጣዩ ዘመን መነሻ ዕቅድ ላይ በአዳማ ከተማ እየመከረ ይገኛል።
የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልቃድር ሁሴን እንደገለጹት፤ 16 ግቦችን የያዘ የክልሉን የትራንስፖርት ሴክተር ሪፎርም ተቀርፆ ወደ ትግበራ ተገብቷል።
በዚህም አዲስ ሶፍትዌር በማበልጸግ የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቡራዩ፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆና አዳማ ከተሞች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።
በተለይ የክፍያ፣ የተሽከርካሪ ስምሪት፣ የመንጃ ፍቃድ እድሳት፣ የጥፋተኝነት ምዝገባ፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ፍተሻና የቦሎ አገልግሎት በአንድ መስኮት እንዲሰጥ የሚያስችል ሶፍትዌር በልጽጎ ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸዋል።
የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ በክልሉ ስድስት ከተሞች ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁንም አስረድተዋል።
በቴክኖሎጂ የተደገፈ የትራንስፖርት አገልግሎትና የዘርፉ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ለማቀላጠፍ የዘመናዊ መናኸሪያዎች ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለዚህም 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተመድቦ የ11 ዘመናዋ መናኸሪያ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የትራፊክ አደጋ ቅነሳና የትራንስፖርት ደህንነት ላይ በሪፎርሙ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!