መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገር ሕልውና ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ የጀመረውን ርብርብ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በከፈተው ጦርነት በየደረሰበት የአማራ ግዛት ሁሉ ንፁሃንን በመግደል፣ ሴቶችን አስገድዶ በመድፈርና የአርሶ አደሩን ጎተራ በመዝረፍ የአማራና የአፋርን ህዝብ እያጎሳቆለ መሆኑን የአማራ ብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ።
የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ የሀገራዊ ሕልውና ዘመቻውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጠላት የሆነው አሸባሪው ህወሓት የአማራ ህዝብን ከምድረ ገፅ ለማጥፋትና ኢትዮጵያንም ለመበታተን አልሞ ጦርነት መክፈቱን የተናገሩት አቶ አብርሃም ንፁሃንን ከመግደልና ዘረፋ ከመፈፀም ጀምሮ ሴቶችን እስከመድፈር የደረሱ ጥቃቶችን በአማራ እና በአፋር ህዝብ ላይ አየፈፀመ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ እንዲሁም የሌሎች ክልሎች ልዩ ኃይሎች በአሸባሪ ቡድኑ የተከፈተውን ጦርነት በጀግንነት እየመከቱ መሆኑንም ገልፀዋል።
የአማራ ህዝብ ሁሉም ፋኖ ነው ያሉት አቶ አብርሀም የአማራ ክልል መንግሥት ላስተላለፈው የክተት ጥሪ ምላሽ በመስጠት ወጣቱ በብዛት ወደ ግንባር እየከተተ መሆኑንም ተናግረዋል።
የክልሉን መንግሥት የክተት ጥሪ ተከትሎ የተደቀነውን የሕልውና ስጋት ለመመከት ህብረተሰቡ በልዩ ልዩ መልኩ እያደረገ ላለው ድጋፍ የአማራ ክልል መንግስት ታላቅ አክብሮትና አድናቆትም አለው ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
በቀጣይም በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅበትን ሁሉ በማድረግ ሀገርን የማዳን ተግባር መፈፀሙን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አቶ አብርሃም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!