የደቡብ ክልል በበልግ ያጣውን 35 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ለመተካት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 21፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል በበልግ ወቅት ያጣውን 35 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ለመተካት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
በደቡብ ክልል በበልግና የመኸር ወቅት የሚመረተው የምርት መጠን 50 በ 50 ድርሻ ቢኖረውም በልግ ላይ በነበረው የዝናብ መዘግየትና ተመልሶ መጥፋት የምርት እጥረት ማስከተሉን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡
በሐምሌ ወር እየታየ ባለው ዝናብ የክልሉ አርሶ አደር ከፍተኛ መነቃቃትን አሳይቷል ያሉት የቢሮ ሃላፊው÷ ምርታማነትን በማሳደግ በበልግ ወቅት የታጣውን 35 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ለመመለስ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ እየተሰራ ያለዉ የችግኝ ተከላ እየታየ ላለው የምርታማነት እጥረት ላይ ያለው አወንታዊ አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በእንስሳት እርባታ ላይ ትኩረት እንዲሰጥና ውጤት እንዲመጣ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራልም ነው ያሉት፡፡
የደቡብ ክልል ማዕከላዊ ዞኖች የመሬት ጥግግታቸው ከፍተኛ በመሆኑ የወተት ምርትን ማሳደግ የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስራውን ለማሳካትም የመኖ እጥረት እንዳይከሰት የሚተከሉት ችግኞች ይህን ያማከሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በክልሉ የፍራፍሬ ልማት ፈጣን ምርት ስለሚሰጥ ከውጪ የሚገቡ የጭማቂ ምርቶችን ለማስቆም እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በመቅደስ አስፋው