ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ የትንሣኤን በዓል ስናከብር ለችግር የተዳረጉ ወገኖችን በማገዝ ቀኑ ለሁላችንም ፍፁም ብርሃን ሆኖ ይውል ዘንድ ክርስቲያናዊ ግዴታችንን መወጣት አለብን ብለዋል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን ሲያበስረን የትንሣኤ ሰዎች ሆነን በመንፈስና በሞራል በማደግ ብርሃናተ ዓለም ልንሆን እንጂ እንደገና የጨለማው ኃይል መሳሪያዎች ልንሆን አይደለም ብለዋል፡፡
የሞቱና የትንሣኤውን ምስጢር በንጹህ ህሊናችን ካስተዋልነው ውስጣችን እሱን ለመቀበል የሚያዳግተው ነገር አይኖርም ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ሁላችንም በፈጣሪ መልካም መንገድ ልንጓዝ ይገባል ሲሉም አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ ካለው በማካፈል የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስና የዕለቱ ደስታ ተካፋይ እንዲሆኑ በማድረግ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በልደቷ ታመነ