Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሃትን ለማጥፋት ወታደራዊ ማሰልጠኛ ለገቡ ዘማቾች የኪነ ጥበባዊ ስራዎች ይቀርባሉ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 7፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሃትን ለማጥፋት ወታደራዊ ማሰልጠኛ ለገቡ ዘማቾች፣ ለአገር ፍቅር መዝመት ክብርና መታደል መሆኑን የሚያሳዩ የኪነ ጥበባዊ ስራዎች ይቀርባሉ።
የብሄራዊ የኪነ ጥበብ አስተባባሪ ኮሚቴ አባልና የኪነ ጥበብ ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ÷ኪነ ጥበብ በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን ለመጠበቅ የማይተካ ሚና ማበርከትን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በገጠሟት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች፣ በመከራም በደስታም ክስተቶች ከያኒያን ለአገራቸው ሕልውና እና ሉዓላዊነት መከበር በጥበባቸው ደጀን ሆነዋል።
በየብሄረሰቡ መልከ ብዙ ባህላዊ የስነ ጥበብ ስራዎች እንዳሉ ገልፀው፤ በዘመናዊት ኢትዮጵያም አገር ስትወረር፣ ሉዓላዊነቷ ሲደፈር ኪነ ጥበብ ማህበረሰቡን በማነቃቃትና ሠራዊቱን በማጀገን ትልቅ ሚና መጫወቱን ነው ያብራሩት።
በአድዋ ጦርነት የአዝማሪዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ጠቁመው፣ በፋሺስት ኢጣሊያ ሁለተኛ ወረራ የአገር ፍቅር ማህበር የነበረው አርበኞችን የማነቃቃት ሙያ አስተዋጽኦውን እንዲሁም በሶማሊያ ወረራ ከያኒያን ደጀን በመሆን የሰሩትን ጀግንነት በአብነት ጠቅሰዋል።
በአሁናዊ የኢትዮጵያ ሁኔታም የአገሪቷን ሕልውና ለመታደግ መከላከያ ሰራዊታችንን በመቀላቀል ማሰልጠኛ የገቡ ወጣቶችን ለማነቃቃት ከያኒያን ደጀን መሆናቸውን በተግባር ለማሳየት ልዩ ልዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ለመመከት ‘ለአገሬ እዘምታለሁ የትም፣ መቼም፣ በምንም’ በሚለው መሪ ሃሳብ በመመራት “የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም ሚናቸውን እየተወጡ ነው” ብለዋል።
በዚህም በውጭ አገር የሚኖሩና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን በአንድ ማዕከል የሚያስተባብር ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደስራ መግባቱን አውስተዋል።
ይህም ለኢትዮጵያ ሕልውና ለሚዋደቀው መከላከያ ሰራዊት አባላት ለአገር ፍቅር መዝመት ክብርና መታደል መሆኑን የሚያሳዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎችን ለማቅረብና ደጀን መሆኑን ለማረጋገጥ በተለያዩ መንገዶች ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በዚህ ተልዕኮም በነገው ዕለት በመጀመሪያ ዙር በርካታ ከያኒያን ወደ ተለያዩ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች እንደሚሰማሩ ነው ያብራሩት።
በቀጣይም ተመሳሳይ ስምሪቶች እንደሚኖሩ ገልፀው፤ በወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ብቻ ሳይሆን አጥንት ለሚከሰክሱትና ደማቸውን ለሚያፈሱት የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች በሚገኙበት ግንባር በመዝለቅም ኪነ ጥበባዊ ስራዎች እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
በውጭም በአገር ውስጥም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን “አገር አትፈርስም” በሚል ለአገራቸው ህልውና ዘመቻ እያገዙ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ በባህልና ቱሪዝም ተደራጅቶ እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ሊሰራበት እንደሚገባም አመልክተዋል።
ሌሎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም በተደራጀ መልኩ አገር የገጠማትን ፈተና በየደረጀውና በተለያየ ኪነ ጥበባዊ ስልት እውነታውን ለማህበረሰቡ በማቅረብ ማነቃቃትና ማስገንዝብ ይኖርባቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.