የመረዳዳትና የመተባበር ባህላችንን አጠናክረን የሀገራችንን ህልውና መጠበቅ አለብን-ዶ/ር ሂሩት
አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን የመረዳዳትና የመተባበር ባህላችንን አጠናክረን የሀገራችንን ህልውና መጠበቅ አለብን ሲሉ የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ተናገሩ።
የሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች እና ሰራተኞች በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት የ2013 የአረንጓዴ አሻራ እና የክረምት በጎ ፈቃድ ማጠናቀቂያ አካሂደዋል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሠራተኞች በከተማ በመገኘት ችግኝ ተከላ እና የከተማ ጽዳት ያከናወኑ ሲሆን፤ በከተማዋ የሚገኙ የአቅመ ደካማ ነዋሪዎችን ቤት እድሳት አስጀምረዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ሠራተኞች የሚካሄደውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ሰፊ ተሳትፎ አድርገዋል።
በአፋር ክልል የክረምቱ ወቅት ዘግይቶ የሚገባ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩን ለማካሄድ ይህን ጊዜ መርጠናል ነው ያሉት።
በመርሃ ግብሩ ሀገር በቀል እና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች መተከላቸውንም ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የተቋሙ ሠራተኞች የገበታ ለሀገር ስፍራዎችን ጨምሮ በሁሉም የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ ችግኝ መትከላቸውን አንስተዋል።
ሚኒስቴሩ በአዋሽ ሰባት ከተማ የሚኖሩ አቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት አፍርሶ የመስራት ስራ ማስጀመሩንም ጠቁመዋል።
የአካባቢው ወጣቶች በመተባበር እና በመደጋገፍ እያከናወኗቸው ያሉት ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያውያን ይህን የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ባህላችንን ማስቀጠል አለብን” ሲሉም አክለዋል።
የአዋሽ ሰባት ከተማ ከንቲባ አቶ ኢብራሂም መሃመድ በበኩላቸው÷ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በከተማዋ ከ150 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎች በየቤታቸው ችግኞችን እንዲተክሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜ ዘግቧል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሠራተኞች በከተማዋ በመገኘት ላከናወኑት በጎ ተግባርም ምስጋና አቅርበዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን