Fana: At a Speed of Life!

የአረንጓዴ ዐሻራ ብሔራዊ ሥራችን ከተፈጥሮ የመታረቅና በልማት የመላቅ አዲስ ጎዳና ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ ብሔራዊ ሥራችን ከተፈጥሮ የመታረቅ እና በልማት የመላቅ አዲስ ጎዳና ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጉዳዩን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የአረንጓዴ ዐሻራ ብሔራዊ ሥራችን ከተፈጥሮ የመታረቅና በልማት የመላቅ አዲስ ጎዳና ነው ብለዋል፡፡

ለአንዲት ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሕዝብ ተደምረን በሠራነው የአረንጓዴ ዐሻራችን፣ ልምላሜ የተራቡ ተራሮች አረንጓዴ ለብሰዋል፤ ምንጮች እና ተፋሰሶች ምድሩን አረስርሰዋል ነው ያሉት።

በረሃማነት ይጸናባቸው የነበሩ ክበበ ምድሮች ነፋሻማ ሆነዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የተፈጥሮን ጫና ተቋቁመናል፤ ይህ ደግ የተፈጥሮ ዕርቅ ነው ሲሉም አውስተዋል፡፡

የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥን ከተፈጥሮ ጥበቃ ጋር በማስተሣሠር በተሠራው ሥራ የፍራፍሬ ተክሎች በስፋት ለምተው ፍሬ መስጠት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም በምግብ ራስን ለመቻል ለጀመርነው ብሔራዊ ኢኒሼቲቭ ተደማሪ ዐቅም መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያ ልጆች ከፖለቲካ አሰላለፍ አልፈው፣ ከሐሳብ ተቃርኖ ተሻግረው፣ ገጸ ብዙ ልዩነቶችን አሸንፈው ለሀገርና ለትውልድ አስበው ያሳኩት የመተባበር ድል፣ የተጨበጠ ማሳያ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ልጆች ስንተባበር ትርፋችን እልፍ፣ ዕቅዳችንም የተሳካ የሠመረ ይሆናል፤የዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ የእስከ ዛሬ ድካማችን መደምደሚያ፣ የድላችን መዳረሻ፣ በድል ላይ ቆመን ለሌላ የላቀ ድል የምንነሣበት ልዩ ዓመት ነው ብለዋል።

ሁላችንም በሩጫ ትግል ሊያልቅ ሲል እንደሚበረቱት ሊጠናቀቅ ሲል እንደሚፈጥኑት ጀግኖች አትሌቶቻችን ካለፉት ዓመታት አስበልጠን እንትከል፣ እንበርታ፣እንፍጠን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.