Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሃትን ወደስልጣን ለመመለስ የሚደረግ የውጭ ጫና የኢትዮጵያውያንን ድምጽ ካለማክበር የመነጨ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) “እጅ በመጠምዘዝ አሸባሪው ህወሃትን ወደስልጣን ለመመለስ የሚደረግ የውጭ ጫና የኢትዮጵያውያንን ድምጽ ካለማክበር የመነጨ ነው” ሲሉ የስድስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተደረጉ ምርጫዎች በተለየ ሁኔታ ሰላማዊ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ተከናውኗል።

ኢትዮጵያውያን ያለማንም ቀስቃሽ ዝናብ፣ ፀሀይና ብርድ ሳይበግራቸው “ይሆነኛል” ያሉትን ፓርቲ በነጻነት መምረጣቸውም ይታወሳል።

በምርጫው ከኢትዮጵያውያን መንግስት የመመስረት ይሁንታ ያገኘው የብልጽግና ፓርቲ ደግሞ በተያዘው መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም አዲሱን መንግስት ያዋቅራል።

የጠቅላይ ሚኒስትርና የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አህመድ ፓርቲያቸው በሚያዋቅረው አዲሱ መንግስት ውስጥ በምርጫው የተሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደተሳትፏቸው መጠን ከታችኛው የመንግስት መዋቅር ጀምሮ በመንግስት አደረጃጀት ውስጥ እንደሚካተቱ መግለጻቸውም አይዘነጋም።

በዛሬው እለትም በምርጫው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው ያሸነፉ የፓርላማ አባላት የሕዝብ ተወካዮች ሚና፣ የአባላት ስነ ምግባር ደንብ እና በምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ወስደዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የስድስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ አባላት እንዳሉት÷ ምዕራባውያን የህዝብ ይሁንታ ያገኘውን መንግስት እጅ በመጠምዘዝ አሸባሪው ህወሃትን ለመመለስ ጫና እያደረጉ ነው።

ይህም የኢትዮጵያውያንን ድምጽ ካለማክበር የመነጨ አካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥረቱም ፈጽሞ ሊሳካ እንደማይችል ተናግረዋል።
ዶክተር ዲማ ነጋዎ “ምዕራባውያን በየመን ካለው አስከፊ ቀውስ ይልቅ ስለ ኢትዮጵያ አብዝተው ይጨነቃሉ ይህም ከሰብዓዊነት ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ እንደሚያሳድዱ ያሳያል” ብለዋል።

“አሸባሪው ህወሃት መስዋዕትነት በተከፈለበት ትግል ከኢትዮጵያውያን ጫንካ ላይመለስ ተወርውሯል”ያሉት ዶክተር ዲማ÷ ምዕራባውያን ይህን ጨቋኝ ቡድን መልሶ በኢትዮጵያውያን ትክሻ ላይ ለመጫን የሚደረጉት ጫና ተቀባይነት የሌለውና የማይሳካ ሙከራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው÷ “የኢትዮዮጵያ ህግ የህወሃትን ቡድን በአሸባሪነት ፈርጇል፤ ይህም ትክክለኛና አግባብነት ያለው ውሳኔ ነው” ብለዋል።

በመሆኑም አሸባሪውን የህወሃት ቡድን ለመመለስ የሚደረግ የውጭ ጫና በራሱ ሽብርተኝነትን ማበረታታት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ምዕራባውያን አሸባሪ ብለው ከፈረጇቸው ቡድኖች ጋር ፈጽሞ እንደማይደራደሩ ሁሉ “ኢትዮጵያንም በዚህ ልክ ሊገነዘቧት ይገባል ነው” ያሉት።

በተለይ “ለሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ተቆርቋሪ ነን ከሚሉ ሀገሮች ይህን አንጠብቅም” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወዳጅ ምዕራባውያን ሀገራት ቢችሉ ሊያግዙን ካልሆነ ደግሞ “ሉዓላዊነታችንን ሊያከብሩ ይገባል ነው” ያሉት።

“ኢትዮጵያውያን በድምጻቸው የሚበጃቸውን መርጠዋል፤ ይህንን ውሳኔ የትኛውም አካል ሊያከብረው ይገባል” ያሉት ደግሞ ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና ናቸው።

በመሆኑም አሸባሪውን የህወሃት ቡድን ለመመለስ የሚደረግ የውጭ ጫና የኢትዮጵያውያንን ድምጽ ካለማክበር የመነጨ መሆኑን እርሳቸውም ይስማማሉ።

ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን በማጠናከር አሸባሪ ቡድኑን እስከወዲያኛው ላይመለስ መቅበር እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

ሌላኛዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ሙስሊማ ረሸድ÷ ምዕራባውያን ከእናንተ ይልቅ እኛ እናውቅላችኋላን ወደ ሚል ያልተገባ ጫና መግባታቸውን አንስተዋል።

ኢትዮዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ምን እንደሚከናወን ነቅተው እየተከታታሉ መሆኑን ገልጸው÷ ከዚህ አኳያ “የምዕራባውያን ጫና ፈጽሞ ሊሳካ አይችልም” ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን እየጨፈጨፈ ካለው አሸባሪው የህወሓት ቡድን ይልቅ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር እየተከተለ ባለው የተዛባ አካሄድ በርካታ ኢትዮጵያውያን ቁጣቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.