የመስቀል በዓል በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃይማኖታዊ ክዋኔው ከሃገር ባህልና እሴት ጋር የሚንጸባረቅበት የመስቀል በዓል ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
ከተማ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በበዓሉ አከባበርና የፀጥታ ሁኔታ ዙሪያ ምክክር አካሂዷል።
የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በዚህ ወቅትባደረጉት ንግግር፥ የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ቢሆንም የሀገርን ባህል፣ እሴትና ትውፊት የበለጠ አጉልተን የምናሳይበት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥተን በጥንቃቄ ልናከብረው ይገባል ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት ቡድን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በከፈተው ወረራና ውጊያ የፀጥታ ስጋት ቢኖርም ህገወጥ ድርጊቶችና ጥቃቶች በሰርጎ ገቦች እንዳይፈፀሙ፥ ሁሉም የፀጥታ ሃይሎች ከወትሮው የተለየ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
የማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ሀገረስብከት ስራ አስኪያጅ አባ ዮሴፍ ደስታ በበኩላቸው÷ የመስቀል በዓልን ስናከብር ክርስቶስ ለሰው ልጆች የዋለውን ውለታ በማሰብ በመተባበርና በመረዳዳት ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በየአካባቢው ለበዓል ማክበሪያ ተብሎ በማህበረሰቡ የሚሰበሰብ ገንዘብም በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ወገኖች ሊለገስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የጥናትና እቅድ ዝግጅት ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ካሳው ጀምበር ባቀረቡት የውይይት መነሻ ፅሁፍ ÷ባለፈው ዓመት የተከናወኑ የፀጥታ ተግባራትን በመገምገምና ከድክመቶች በመማር የተደራጀና የተጠናከረ የደህንነት ስራ ለመስራት ዝግጅቶች ተጠናቅቀዋል ብለዋል።
በነብዩ ዩሃንስ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!