በቦንጋ ከተማ ሲካሄድ የዋለው የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት በሰላም ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ-ውሳኔ በአምስት ዞኖችና በአንድ ልዩ ዞን ያሉ ህዝቦች ዛሬ ከማለዳው 12 ሰአት ጀምሮ ድምጻቸውን ሲሰጡ ውለዋል።
በሕዝበ-ውሳኔው የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምእራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ የዳውሮ ዞን እና የሽካ ዞን “ከደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል መመስረታቸውን እደግፋለሁ” እና “የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አካል ሆነው መቀጠላቸውን እደግፋለሁ” በሚሉት ውሳኔዎች ላይ ነው ድምጻቸውን ሲሰጡ የዋሉት።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የዞኑ ተወላጆች የሆኑ ምሁራን፣ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የስራ ሀላፊዎችና ባለሀብቶች ከተለያዩ ቦታዎች መጥተው ድምጽ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የህዝበ ውሳኔ ማስተባበሪያ የቦንጋ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ነጋሳ የምርጫውን ሂደት አስመልክቶ እንደገለጹት፥ በደቡብ ክልል በአምስት ዞንና በአንድ ልዩ ወረዳ ሲካሄድ የዋለው የድምጽ መስጠት ሂደት በአብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች መጠናቀቃቸውን ሪፖርት እንደደረሳቸው ገልጸዋል።
በዝናብ ምክንያት በዳውሮ ዞን አሁንም በአንዳንድ ጣቢያዎች ሰልፎች አሉ ያሉት አስተባባሪው፥ ሰልፍ ላይ ያሉ ሰዎች እስኪጭርሱ ምርጫ ጣቢያዎች ክፍት ሆነው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ምርጫውን በተመለከተ ያጋጠመ የሰላም ችግር የለም፣ ካርድ የወሰዱ መራጮች በአብዛኛው ድምጻቸውን ሰጥተዋል ነው ያሉት።
ምርጫ በተጠናቀቀባቸው ጣቢያዎች ወደ ቆጠራ እየገቡ ሲሆን፥ በነገው እለት በየምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ ውጤት ይለጠፋሉ ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!