130 ሚሊየን ሕዝብ መሸከም የሚችል አውድ ለመፍጠር ተቋማት ግንባታ ላይ ሰርተናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 130 ሚሊየን ሕዝብ መሸከም የሚችል አውድ ለመፍጠር ተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥተን ሰርተናል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁልፍ የመንግሥት ፋይናንስና ሌሎች የፋይናንስ ዘርፍ ተቋማትን ያሰባሰበው ‘የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ’ ኮንፈረንስ ላይ የእሳት ዳር ወግ ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም በሰጡት ማብራሪያ፤ የተቋማት ሪፎም እና ተቋማት የማደረጀት ጉዳይ መነሻው ፍላጎት እንደሆነ እና ተቋማት ማለት ሀሳቦቻችን ከእኛ ባሻገር ለብዙኃን መድረስ እንዲችሉ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
ተቋም ውስጥ መታየት ካለባቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል ታማኝነት፣ ግልጸኝነት፣ ተጠያቂነት፣ የተራጀ ከሆነ ጠንካራ፣ ራሱን የሚያሻሽል እና የሚላመድ በመሆን ሀሳብን ብዙኃን ጋር እንዲደርስ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
የፋይናንስ ዘርፉን ለመለወጥ ስራ ሲጀመር በፖሊሲ፣ በስትራቴጂ፣ በአመራር፣ በአሰራር መዘመን የሚፈልጉ ተቋማት እንደነበሩ አስታውሰዋል።
አንዳንድ ተቋማት ደግሞ መኖር ሲገባቸው እንዳልተፈጠሩ አንስተው፤ አዲስ ተቋምት በማዋቀር አዳዲስ አሰራሮች እና አዳዲስ አመራሮችን ይዘው መጥተዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እየዘመነ ባለበት መንገድ እንደዚህ ዓይነት ተቋማት ካልተገነቡ በቀር ተሻግሮ ተጽዕኖ ማምጣት አይቻልም ነው ያሉት።
የተቋም ግንባታ ያሉትን ማዘመን የሚጎሉትን መሙላት ዘመን በሚዋጁበት አግባብ መስራት እና ማዘጋጀት ህልም ካለው ማንኛውም ሀገር እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ስለሆነም ተቋማት ግንባታ ላይ በትኩረት መሰራቱን አብራርተዋል።
በፋይናንሱ ብቻ ሳይሆን ደህንነት፣ ሳይበር እና ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች ላይ ለትውልድ እጅግ አስፈላጊ የሚባሉ ተቋማትን መፍጠር ላይ መሰራቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ፣ የኢትዮጵያን ስፋት እና ከ130 ሚሊየን በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መሸከም የሚችል አውድ ለመፍጠር ካለን መሻት የተነሳ ተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥተን ሰርተናል ብለዋል።
በዮናስ ጌትነት