ሃገራችንን በጋራ ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል- ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሾሙ የካቢኔ አባላት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በአዲሱ የአስፈጻሚ አካል ስልጣን ማጋራቱ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መተማመን በመፍጠር ለሃገር ችግር የጋራ መፍትሄ ለማምጣት ትልቅ ዕድል የሚሰጥ ነው የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የኦነግ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ።
ሁለቱ መሪዎች አዲስ በተዋቀረው የአስፋጻሚ አካል በሚኒስትርነት መሾማቸውን ተከትሎ÷ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ህዝብና መንግስት የሰጣቸውን ሃላፊነት በተመደቡበት ቦታ የተሻለ ስራ በመስራት ውጤት ለማምጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የኢዜማ መሪ ፕሮፎሰር ብርሃኑ ነጋ በትምህርት ሚኒስትርነት መሾም የፈጠረባቸው ደስታ ገልፀው÷ የኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ፋንታ የሚወሰነው የትምህርት ጥራት በማስጠበቅ እና የሃገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ማስተካከል ስንችል ነው ብለዋል።
ለዚህም የተረጋጋ ማህበረሰብ እና ተወዳዳሪ ዜጋ እንዲኖረንም ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ቀዳሚ ስራዬ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
መንግስት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ስልጣን ማጣቱ አሁን ያሉ ችግሮችን እና ነገ የሚያጋጥሙ ፈተናዎች እንደሃገር በጋራ ለማለፍ ያስችላል ብለዋል፡፡
በቀጣይ እንደ ሃገር ለሚደረገው ብሔራዊ መግባባት ውይይቶች መተማመን በመፍጠር ለችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ ለመስጠት ያስችላል ነው ያሉት።
በባህል እና ስፖርት ሚኒስትርነት የተሾሙ ሌላኛው የኦነግ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው÷ የእኔ መንገድ ብቻ ነው ትክክል የሚል የፖለቲካ ባህል ሃገርንም ህዝብንን ጎድቶ ቆይቷል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የገቡትን ቃል ወደ ተግባር በመቀየር የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንዲራመድ ማድረግ ችለዋል ነው ያሉት።
አስቀድመው በተቋቋሙ የክልል መንግስታት የተፎካካሪ ፓርቲዎች መካተታቸውን ስንመለከትም በሃገሪቱ ፖለቲካ ተስፋ እንድንጭር አድርጎናል ብለዋል፡፡
በአዲስ የፖለቲካ ባህል የሚገጥሙ ፈተናዎች በመሻገር የጋራ ሃገራችንን በጋራ ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል ሲሉ አዲስ የተሸሙት ሚኒስትሮች ተናግረዋል።
በበላይ ተስፋዬ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!