Fana: At a Speed of Life!

ለስኳር ህሙማን ኢንሱሊን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) ለስኳር ህሙማን ኢንሱሊን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ እንደሚችል “አይ ኬር” የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።
ፕሮጀክቱን ይፋ ያደረጉት የስኳር ህሙማን ማህበር፣ የጤና ሚንስቴር ፣ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ እና ‘ኖቮ ኖርዲስክ’ የተባለ የዴንማርክ መድሃኒት አቅራቢ ድርጅት በጋራ በመሆን ነው፡፡
ፕሮጀክቱ በቀጣይ ሶስት ዓመታት በስኳር ህሙማን የመድሃኒት አቅርቦት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ነው ተብሏል።
የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ የሚገኙ የስኳር ህሙማን ኢንሱሊን የተባለውን መድሃኒት በተመጣጣኝና አነስተኛ ዋጋ እንዲያገኙ ማስቻል ነው ተብሏል።
ማህበሩ እድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ለሆኑ የስኳር ህሙማን ያለምንም ክፍያ መድሃኒቱን እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤በፕሮጀክቱ አማካይነት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና ህክምናውን በቅርበት ለማያገኙ ዜጎች ኢንሱሊን በዝቅተኛ ዋጋ ተደራሽ እደሚሆን ተናግረዋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ሰለሞን በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከኢንሱሊን አቅርቦት በተጨማሪ የመመርመሪያ መሳሪያዎች አቅርቦት እና የስኳር ህመም ግንዛቤ ማሳደግ ስራ ማካተቱን ገልጸዋል።
ሚንስቴሩ በጤናው ዘርፈ ያለውን ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በተቀናጀ መልኩ የሚመራበት ፖሊሲ ቀርጾ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢንሱሊን ወደ ሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ እንዲገባ በመንግስት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱ የኢንሱሊን አቅርቦትን በማሻሻል ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የጤና ተደራሽነትና ጥራት ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት የዴንማርክ መንግስት እንደሚደግፈው የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ኪራ ስሚዝ ናቸው፡፡
ፕሮጀክቱ የኢንሱሊን አቅርቦትን በማሳደግ በስኳር ህመም ሳቢያ የሚደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት በመቀነስ ረገድ የማይተካ ሚና አለው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።
በኢትዮጵያ 1 ሚሊዮን 700 ሺህ ሰዎች ከስኳር ህመም ጋር እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.