ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአዲሱ ካቢኔ መካተታቸው የሀገሪቱን እድገትና አንድነት ያጠናክራል- የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የሚኒስትሮች ሹመት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካተታቸው የሀገሪቱን ዕድገትና የሕዝቦችን አንድነት እንሚያጠናከር የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ሹመቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለአገራቸው ሰላምና ብልጽግና በአንድነት እንዲቆሙ ያነሳሳቸዋል ሲሉ ነው ነዋሪዎቹ አሰተያየታቸውን የገለጹት።
ከነዋሪዎቹ መካከል ኮማንደር ኡማን ኡጋላ በፓርላማ ደረጃ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በአካተተ መልኩ የተሰጠው ሹመት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ጭምር ተምሳሌት ነው ብለዋል።
ባልተለመደ መልኩ በአብላጫ ደምጽ አሸንፎ መንግሥት የመሰረተው ብልጽግና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በአስፈፃሚው አካላት እንዲካተቱ ማድረጉ ሀገራዊ አንድነትን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
በአስፈፃሚው አካል የተካተቱ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት ከመንግሥት ጎን በመሆን ለሀገርና ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም መከበር ሲሰሩ እንደነበር ጠቅሰዉ÷ይህም ለአገር ሰላምና ልማት ተባብረው እንደሚሰሩ ያሳያል ብለዋል።
በኢትዮጵ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊሾሙ ቀርቶ በሀገር ውስጥ በሰላም የማይኖሩበት ሁኔታ እንደነበር በማስታወስ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ አቶ ኒይና ኦኬሎ ናቸው።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአስፈፃሚ አካላት እንዲካተቱ መደረጉ ታላቅ የፖለቲካና የለውጥ ምዕራፍ መሆኑንም አስረድተዋል።
ሹመት የዳር ተመልካችነትንና ትችትን በመተው ለሀገር ሰላምና ብልጽግና በአንድነት እንዲቆም ያደረጋል ብለዋል።
ሚኒስትሮቹ ሀገሪቱ ያሉባትን በተለይም የሰላም፣ የኑሮ ውድነቱንና የሥራ አጥነት ችግሮ ይፈታሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ነው አቶ ኒይና የተናገሩት።
ሌላው የቀድሞው የባህር ኃይል አባል አቶ ኡሞድ ኡሜት በበኩላቸው፥ ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው የፖለቲካ መዋቅር ብሄርን መሰረት ያደረገ ስለነበር ግጭቶች ተበራክተው እንደቆዩ ያስታውሳሉ።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማካተት የተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሹመት የቀድሞውን መጥፎ ታሪክ በመሻር የልማትና የብልጽግና ጉዞውን የሚያፋጥን ነው ማለታቸዉን የዘገበዉ ኢዜአ ነዉ።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!