Fana: At a Speed of Life!

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአሸባሪው ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖች 10 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ባቋቋሙት የአስቸኳይ ጊዜ ገንዘብ አሰባሰቢ ኮሚቴ አማካኝነት የተሰበሰበ 10 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው ምግብና አልባሳት በአሸባሪው የህውሃት ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ።

ኮሚቴው በአሜሪካና አውሮፓ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደተቋቋመ ተገልጿል።

ድጋፉን ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተገኝተው ያስረከቡት የኮሚቴው ተወካይ አቶ ጌታቸው በየነ በወቅቱ እንዳሉት፤ ኮሚቴው በአሸባሪው ቡድን ወረራ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

በአጭር ጊዜ ውስጥም ከለጋሾች ሀብት በማሰባሰብ በመጀመሪያው ዙር በወሎ አካባቢ ተፈናቅለው ለሚገኙ ዜጎች 12 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገበት 1 ሺህ 500 ኩንታል ዱቄት፣ አልባሳትና አልሚ ምግቦች ድጋፍ መደረጉን አውስተዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ በባህር ዳር፣ እብናት፣ጋይንት፣ ደባርቅ እና ዳባት ለሚገኙ ተፈናቃዮች 10 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገባቸው አንድ ሺህ ኩንታል የምግብ ዱቄት፣ አልባሳትና አልሚ ምግብ እንዲደርሳቸው መመቻቸቱን አስታውቀዋል።

ተጎጂዎችን የመደገፉ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ በቀጣይ ደግሞ ለህክምና ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችና የአልባሳት ድጋፍ በጦርነቱ ለተጎዱ የፀጥታ አባላት ጭምር እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለተገዱ ወገኖች ፈጥኖ በመድረስ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

“ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ውለታ ስራ እያከናወናችሁ ነው” ያሉት ደክተር ድረስ፤ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አመልክተዋል።

በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ከአንድ ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች የአካባቢው ህዝብ የእለት ድጋፍ በማቅረብ እየተረባረበ መሆኑንም አስረድተዋል።

በድጋፍ ርክክቡ ስነ-ሰርዓት የባሀርዳር ከተማ አመራሮች፣ የኮሚቴው ተወካዮችና አባላት መገኘታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.