ጠላት ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ከፍተኛ ውድመት አድርሷል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 20 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠላት ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ፥ የማህበረሰቡ የስነልቦና ውቅር ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ሆን ብሎና አቅዶ በእምነት ተቋማትና በቅዱሳት መጻህፍት ላይ ጉዳት ማድረሱንም ተናግረዋል።
በየአካባቢው የሚገኘው ህዝብም ጠላት የሚያደርሰውን ውድመት በመከላከል÷ የሚሸሸውን ጠላት በመልቀምና መረጃ በመስጠት ሊተባበር ይገባል ብለዋል።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ መረጃዎች የሚያሰራጩ ግለሰቦች ህግን በማክበር አገርን እንዲያከብሩም ጠይቀዋል።
ሚኒስትር ዲኤታዋ በመግለጫቸው ከኢትዮ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም ሁለቱ አገራት ዘመናትን የዘለቀ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቅሰው፥ አሁን ላይም የአገራቱን ግንኙነት ግምት ውስጥ ያላስገቡ እንቅስቃሴዎችን ለመመከት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በመገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ በሱዳን ወታደሮች ላይ ጥቃት ፈጽማለች በሚል የተሰራጨው መረጃ ሀሰት መሆኑን ሚኒስትር ዲኢታዋ አብራርተዋል።
የአገራቱን ግንኙነት ለመበረዝ የሚሰራጨው መረጃም መሰረተ ቢስ መሆኑን ነው የተናገሩት።