የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ለተፈናቀሉ ዜጎች 17 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረጉ፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች ግምታቸዉ 10 ሚሊየን ብር የሚሆን የቁሳቁስ እና አልባሳት ድጋፍ አድርጓል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጃዋር እና የድሬዳዋ የአገር ሽማግሌዎች የተሰበሰበውን ድጋፍ ለአፋር ክልል ያስረከቡ ሲሆን ÷ የአፋር ክልል ርዕሰ መሰተዳድር አወል አርባ ከከተማ አስተዳደሩ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት 7 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የሚገመት የዓይነትና የህክምና ግብዓቶች ድጋፍ በህወሓት የሽብር ቡድን ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ ለተጠለሉ ዜጎች ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፎቹን ለደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር እና ለደብረ ብርሃን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያስረከቡት የድርጅቱ አገር ዓቀፍ ተጠሪ አቶ ይልማ ታዬ÷ የተደረገው ድጋፍ የተፈናቃዮችን መሠረታዊ ፍላጎት እና የሆስፒታሉን የግብዓት ክፍተት በመለየት የቀረበ ነው ብለዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አካሉ ወንድሙ÷ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ይህን አርዓያነት እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
መረጃው የድሬዳዋ ከንቲባ ጽህፈት ቤትና የሰሜን ሸዋ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው