“በትግራይ የዘር ማጥፋት ተፈፅሟል” በሚል ኢትዮጵያን ለመወንጀል በአሜሪካ ሲረቀቅ የነበረው አዋጅ ተሰረዘ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር “በትግራይ የዘር ማጥፋት ተፈፅሟል” በሚል ኢትዮጵያን ለመወንጀል ለወራት ሲዘጋጅ የነበረው ረቂቅ አዋጅ በሀገሪቱ ብሄራዊ መከላከያ ፍቃድ ህግ ተሰረዘ።
የ”ትግራይ የዘር ማጥፋት አዋጅ” ማሻሻያ በዚህ የሀገሪቱ ፌደራል ተቋም መወገዱን የኢትዮ-አሜሪካ ልማት ምክር ቤት አስታውቋል።
ይህ ሲ ኤን ኤንን የመሰሉ የሚዲያ ተቋማትን የሀሰት ዘገባዎች መሰረት አድርጎ ሲረቅ የነበረው እና ይፀድቃል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የአዋጅ ማሻሻያ በተቋሙ የተነሳው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሃሽታግ በቃ (#NoMore) ዘመቻ ተደጋጋሚ ግፊቶችን ማድረግ እና ቀጥታ ለሚወክሏቸው የኮንግረስ አባላት ደብዳቤ እና ኢሜይል በመላክ ግፊት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው የአዋጅ ማሻሻያው እንዲቀር የተደረገው።
ምክር ቤቱ ሌሎች የሀሰት ውንጀላዎችን መሰረት አድርገው ኢትዮጵያን ለመጉዳት እየተዘጋጁ ያሉ ህጎች እስከሚተዉ ድረስ ትግሉ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስቧል።