የአንዳንድ መንግስታትን የሀሰት ትርክት ውርጅብኝ በኢትዮጵያውያን ትግል ተቋቁመናል- አምባሳደር ተፈሪ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ የሚዲያና የአንዳንድ መንግስታትን የሀሰት ትርክት ውርጅብኝ በኢትዮጵያውያን ትግል ተቋቁመናል ሲሉ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ ይሄንን ያሉት÷ ‘ኢትዮጵያን እናድን’ በሚል መሪ ቃል በአማራና አፋር ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ ከ370 ሺህ ፓውንድ በላይ ማሰባሰብ መቻሉ በተገለጸበት ወቅት ነው፡፡
በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዲፌንድ ኢትዮጵያ ዩናይትድ ኪንግደም ግብረሀይል ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት÷ መላው ዩናይትድ ኪንግደምን የወከሉ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት መድረክ ነው ይህ የተገለጸው፡፡
ሽብርተኛው ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የደቀነውን ሀገርን የማፍረስ እኩይ ተግባር ለመመከት በቁጭት ተነስተን ይህን የድጋፍ ዝግጅት ማከናወናችን ትልቅ ኩራት መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ የሚዲያና የአንዳንድ መንግስታት የሀሰት ትርክት ውርጅብኝን በኢትዮጵያውያን ትግል ተቋቁመናል ነው ያሉት አምባሳደሩ፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር በሚደረገው ትግል የኢትዮጵያን ድምጽ ለአለም በማሰማት እና የተፈናቀሉ ወገኖችን
ለመርዳት ከ370 ሺህ ፓውንድ በላይ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በከፈሉት መስዋዕትነት አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ አድርገውናል ያሉት ደግሞ÷ የዲፌንድ ኢትዮጵያ ዩናይትድ ኪንግደም ግብረሀይል አስተባባሪ አቶ ዘላለም ተሰማ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጦር ግንባር ድረስ በመሄድ በሰጡት አመራር በአጭር ጊዜ የሀገራችንን አንድነት ያስከበሩ በመሆናቸው እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
የተፈናቀሉ ወገኖችን ከመደገፍ በሻገር ሀገራችን በምትፈልገው ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ ነን ማለታቸውን በእንግሊዝ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡