ሱዳን ያለ ውጪ ጣልቃ ገብነት የራሷን ችግር በራሷ መፍታት ይኖርባታል – የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሱዳን ያለ ማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የራሷን ችግር በራሷ መፍታት እንዳለባት የኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በመግባት ሠላምና መረጋጋት ተስኗት በቀጠለችው ሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ስልጣናቸውን ለቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥቅምት ወር አጋማሽ ከሌሎች ከፍተኛ ሹማምንቶች ጋር በወታደራዊ ኃይሉ በቁም እስር ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገር ሱዳን ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለች መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ሱዳናውያን ያሉባቸውን ልዩነቶች ያለማንም የውጪ ጣልቃ ገብነት በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ኢትዮጵያ ትሻለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሁልጊዜም የምትፈልገውና ማየት የምትሻው የሱዳንን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ነው ሲሉም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሁለቱ ሀገራት የድንበር ጉዳይም በውይይት ብቻ እንደሚፈታ ከዚህ ቀደም ስትገልጽ መቋየቷን አስታውሰው አሁንም ይህንኑ አቋም ይዛ ትቀጥላለች ብለዋል።
ኢትዮጵያና ሱዳን አንድ ሕዝብ ነን፤ የፖለቲካ ድንበሩ ሰው ሰራሽ ነው፤ እኛ ለሚሰነዘሩብን ማንኛውም አይነት ጥቃቶችና ድርጊቶች አሉታዊ የአጸፋ ምላሽ መስጠት አንፈልግም ብለዋል።
ለዚህም አሁን በሱዳን ካለው አስተዳደር በተለይም በሽግግር መንግስቱ የወታደራዊ ክንፍ በኩል እኛን ለግጭት ለማነሳሳት ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ምላሽ ከመስጠት የተቆጠብነው ከዚህ ጉዳይ ጀርባ ሆኖ ግፊት የሚያደርገውን አካል ስለምናውቅ ነው ነበር ያሉት አምባሳደር ሬድዋን።
እ.አ.አ በ2019 የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አል-በሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህምድ አማካኝነት የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ወሳኝ ሚና ተጫውታለች።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!