ኅብረ ብሄራዊ አንድነታችንን በማጠናከር አገራዊ ተግዳሮቶችን በድል እንሻገራለን – የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ም/ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኅብረ ብሄራዊ አንድነታችንን በማጠናከር አገራዊ ተግዳሮቶችን በድል እንሻገራለን ሲሉ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ፡፡
አመራሮቹ “በዘላቂ ድል ወደ ብልጽግና እንዲሁም የድህረ ጦርነት መዛነፎችና እርምቶች” በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ለሁለት ቀናት ያደረጉት ውይይት ተጠናቋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በውይይቱ ማጠቃላያ ላይ እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ በአገር ውስጥና በውጭ ኃያላን አገራት ከተቃጣባት የህልውና አደጋ በመላው ኢትዮጵያዊያን ርብርብ በድል መውጣት መቻሏን ገልጸዋል፡፡
እንደአገር በተሰራው የዲፕሎማሲ ሥራም ከኢትዮጵያ ጐን ለቆሙ አገራት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የተገኘውን ድል አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግም በውስጥም ሆነ በውጪ በእርስ በርስ ግጭትና የመጠቃቃት አዙሪት ውስጥ ለማስገባት የሚፈልጉ ሃይሎችን በንቃት በመከታተል እኩይ ሴራቸውን ለማክሸፍ የጸጥታ አካላትና መላው ህብረተሰብ በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ- ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው ፥ በጦርነቱ ሂደት ኢትዮጵያ አሸናፊ መሆኗ፣ የመከላከያ ሠራዊትና የክልል ጸጥታ ሃይሎች ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ መስራታቸው፣ በአገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም መላው ህዝብ በጋራ በመቆም ለኢትዮጵያ አሸናፊነት ለከፈሉት መስዋዕትነት እውቅና መስጠት ተገቢ መሆኑን አውስተዋል፡፡
አገራዊ የምምክር መድረኩንም በዚህ ቅኝት ማካሄድ እንደሚገባ ነው አፈ ጉባኤው የጠቆሙት፡፡
የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ ፥ ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር ዘላቂ ሠላም ለመገንባት ጠንካራና የህዝብን ፍላጐት መሠረት አድርጐ የሚንቀሳቀስ መንግስታዊ ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም የምክር ቤት አባላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተቃጣውን አደጋ መላው ህዝብ ያለምንም ልዩነት በአንድነት በከፈለው መስዋዕትነት የጠላትን ፍላጐት መቀልበስ እንዳስቻለ ሁሉ ፤ በቀጣይም የውስጥ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
በቀጣይ በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትና መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋምና የመከላከያ ሰራዊቱን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሠራ አቶ ተስፋዬ እስገንዝበዋል፡፡
በውይይቱ ኅብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር አገራዊ ተግዳሮቶችን ለመሻገር በሚያስችል ደረጃ ለመሥራት የሁለቱ ምክር ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች የጋራ አቋም ላይ ደርሰዋል፡፡
በቀጣይ ወሳኝ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ቀሪ የምክር ቤቶቹ አባላትና የጽህፈት ቤቶቹ ሠራተኞች ውይይት እንደሚያደርጉም ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!