Fana: At a Speed of Life!

የተወሰኑ ሰዎች ክስ መቋረጥ በአውደ ውጊያ ያገኘነው ድል በሰላሙ መድረክም እንዲደገም የሚያግዝ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘላቂ ድል ለማረጋገጥ በጀግንነት ተዋግቶ ህይወትን ገብሮ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ከእኔ ይቅር ብሎ ለተሸናፊ ይቅርታን መስጠት የአባቶቻችን ታሪክ መሆኑን ማስታወስ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ምረቃ እና ልዩ የጀግንነት ተግባር ለፈፀሙ የሠራዊቱ አባላት በተዘጋጀ የሽልማትና ዕውቅና ስነስርዓት ላይ ነው፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ በንግግራቸው ÷የኢትዮጵያን ሥም ለማደስ እጅግ ከፍተኛውን ጀግንነት እና ብቃት ላሳዩ ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ለአሸነፈ ሽልማትን ለተሸነፈ ደግሞ ምህረትን ማድረግ ከአባቶቻችን የተማርነው ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለኢትዮጵያ የሚበጅ እና ዘላቂ ጥቅምን የሚያግዝ በአውደ ውጊያ ያገኘነውን ድል በሰላሙ መድረክም እንዲደገም የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህም በመሆኑ መላው ኢትዮጵያውያን ለሃገራችሁ ክብር እና አሸናፊነት ስትሉ ይህንን ውሳኔ እንድትቀበሉ በትህትና እጠይቃለሁም ነው ያሉት፡፡

መንግስት የተወሰኑ ሰዎችን ክስ ማቋረጡ የኢትዮጵያን ጠላቶች ለመቀነስ፣ ጉልበት ለመሰብሰብ እና ጥፋተኛ ከጥፋት ጎዳናው እንዲመለስ ለማስቻል መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

ይቅር ማለታችን በማሸነፋችን ያገኘነው ጸጋ ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡

ጠላቶቻችን ቢያሸንፉ ኖሮ የምህረት ልብ አይኖራቸውም ነበር ብለውም፥ ምህረት ለመስጠት ሳይሆን ምህርት ለመቀበል ዕድል አናገኝም ነበር ነው ያሉት፡፡

ይቅር ያልነው መበቀል እና ማሰር እየቻልን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የጠላቶቻችን ባህሪ እና ባህል እኛን እንዲወርሰን አንፈልግም ብለዋል፡፡

ውሳኔው ለልጆቻችን የድልና የአሸናፊነት መንፈስ የሚያላብስ፣ አርቆ በማሰብ ኢትዮጵያን በማጽናት ላይ ብቻ መሰረት ያደረገ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ክስ ማቋረጥ ማለት ምህረት ማድረግ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ክስ የተቋረጠላቸው ሰዎች በአግባቡ እድሉን እንዲጠቀሙ መክረዋል፡፡

ስላሸፍን መበቀል እየቻልን ይቅር ያልነው እናንተን ብለን ሳይሆን ከእናት ጀርባ ያለውን ህዝብ ብለን ነውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህወሓት ስህተት የምንማራቸው ብለው ከገለጿቸው ሀሳቦች በመጀመሪያ ደረጃ፥ ቡድኑ ከፋፋይ ሃሳብ፣ ጥላቻ እና ሌብነት ለከፍተኛ ሽንፈት ያበቁት መሆናቸው እንዲሁም ለውጡ እንደመጣ በተደጋጋሚ የይቅርታ በር ቢከፈትለትም በዕድሉ ተጠቅሞ የለውጡን ጉዞ መቀላቀል አለመቻሉን አንስተዋል።

የሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት ህዝቡ እንዲቆጣና በአንድ መንፈስ እንዲዘምት እርጎታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ህወሓት ጉዞው ቁልቁለት ሆነልኝ ብሎ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መጓዙ ስህተቶቹ ነበሩ ብለዋል ፡፡ እኛም ወደ ትግራይ የማንገባው ከቡድኑ ጥፋት ስለተማርን ነው ብለዋል፡፡

አሁንም ህወሓት አላረፈም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰባተኛ ስህተቱ መስመር ስቶ ሳይሄድ መማር የሚችልበት ዕድል መፍጠር የራሱ ቢሆንም እንኳ እንደባላንጣ አትንኩን እረፉ ለማለት እወዳለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ የነካካችሁን እንደሆነ በተለመደው መንገድ የከፋ ቅጣት ይደርስባችኋል ብለዋል፡፡

በኢኮኖሚ ፣ ፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ እጅግ የከፋ ጉዳት የደረሰበት የትግራይ ህዝብም አይኑን እንዲገልጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብም የድላችን ሚስጥር አንድ መሆናችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ሆኖ መቆምንና መደመርን ፈልጉ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.