ዳያስፖራው በሀገር ውስጥ ያለውን ሰፊ እድል በመጠቀም መዋዕለ ንዋያቸውን ሊያፈሱ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአምራች ዘርፉ መሰማራት ከሚፈልጉ ዳያስፖራዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያየ ነው፡፡
በምክክር መድረኩ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፥ በአምራች ዘርፉ ያሉትን እድል በመጠቀም ሀገሪቱ ያለባትን ጉድለት ለመሙላት በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በወጪ-ገቢ ንግድ ሚዛን ወደ 15 ቢሊየን ዶላር ጉድለት አለባት ያሉት ሚኒስትሩ፥ ይህን ለማስተካከል አምርቶ ወደ ገበያ የማቅረብ አቅምን ማሳደግ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ለዚህም በአምራች ዘርፉ ያለውን ሰፊ እድል መጠቀም እንደሚገባ አስረድተዋል፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው÷ የመረጃ እጦት እስካሁን ዳያስፖራው በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋዩን እንዳያፈስ ማድረጉን በአንስተዋል፡፡
አሁን ላይ ለዘርፉ እየተመቻቹ ያሉ ሁኔታዎች ዳያስፖራው በአምራች ዘርፉ እንዲሰማራ እድል የሚሰጡ መሆናቸው ነው የተናገሩት፡፡
የሀገሪቱን ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅ ዳያስፖራው በአምራች ዘርፉ እንዲሳተፍ ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
በውይይቱ በአምራች ዘርፉ ላይ ያሉ እድሎች ምን ምን ናቸው የሚለው ጉዳይ በጥናት እየቀርበ ነው፡፡
በታሪኩ ለገሰ