Fana: At a Speed of Life!

የዳያስፖራው አስተዋጽኦ አሸባሪው ህወሓት ዳግም ስጋት መሆን እስከማይችል ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት – ዶ/ር ይልቃል ከፋለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አሸባሪው ህወሓት ዳግም ስጋት መሆን እንዳይችል ለማድረግ እና በአሸባሪ ቡድኑ የደረሱ ጉዳቶችን መልሶ ለመገንባት የዳያስፖራ አባላት የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠየቁ።
 
በአማራ ክልል የዳያስፖራ አባላት ከክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በባህር ዳር ከተማ እየመከሩ ነው።
 
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ÷ ዳያስፖራው አሸባሪውን የህወሓት ሃይል ለመምታት በተደረገው ርብርብ በልዩ ልዩ መልኩ ያደረገው አስተዋፅኦ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው ብለዋል።
 
የአማራ ህዝብ ህልውና በአስተማማኝ ሁኔታ አስኪረጋገጥ ድረስ የዳያስፖራ አባላት በልዩ ልዩ መልኩ የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ነው የጠየቁት።
 
የአማራ ህዝብን ህልውና በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ የውስጥ አንድነታችንን በማጥበቅ አሸባሪውና ወራሪው የህወሓት ሀይል ምንም ዓይነት ስጋት መሆን እስከማይችል ድረስ ትግላችን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል ዶ/ር ይልቃል።
 
ትግላችን ዘርፈ ብዙ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ጦርነቱ የመጀመሪያው ግንባር ቢሆንም በአሸባሪ ቡድኑ የወደሙና የፈረሱ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ርብርብም ሌላኛው ግንባር መሆኑን ጠቁመዋል።
 
ለዚህም የዳያስፖራ አባላት ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
በምክትል ርዕሰ መስተድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና በአማራ ክልል የዳያስፖራ አቀባበል ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ስዩም መኮንን በበኩላቸው÷ የአሸባሪው ህወሓት ሃይል 7 የአማራ ክልል ዞኖችን በመውረር ዘግናኝ ግፎችን ፈፅሟል ብለዋል።
 
አሸባሪ ቡድኑ በመላ ኢትዮጵያውያን ርብርብ በወረራ ይዟቸው ከነበሩ አካባቢዎች ተጠራርጎ እንዲወጣ ተደርጓል ያሉት አቶ ስዩም÷ በዚህ ትግል የአማራ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተነቃንቆ በአሽባሪ ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ድል ማስመዘገቡን ገልፀዋል።
 
አሁንም አሸባሪ ቡድኑ ለሀገር ስጋት መሆን እስከማይችል ድረስ ትግላችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.