Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ የሀገራችንን በጎ ገጽታ የምንገነባበት ሊሆን ይገባል-አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የሀገራችንን በጎ ገጽታ የምንገነባበት ሊሆን ይገባል ሲሉ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ፡፡
 
ሚኒስትሯ የኅብረቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባን እና የቋሚ መልዕክተኞች መደበኛ ስብሰባን ስኬታማ ለማድረግ ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
በምክክር መድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮ ቴሌኮም፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የእሳት አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ሆቴሎች ማኅበር እና የአስጎብኚ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
 
ውይይቱ የጉባኤው ተሳታፊዎች ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን እና የተቀላጠፈ የመሠረተ ልማት አገልግሎት ማለትም የኢንተርኔት፣ የስልክ፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የትራንስፖርት እና የጉብኝት ፕሮግራም አገልግሎቶች እንዲያገኙ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።
 
አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፥ በአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የሚመጡ የአፍሪካ መሪዎችንና ሌሎች የጉባኤ ተሳታፊዎችን ደረጃውን በጠበቀ መስተንግዶ በመቀበል የሀገራችንን በጎ ገጽታ የመገንባት የዜግነት ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን ብለዋል፡፡
 
እንግዶችን በላቀ መስተንግዶ ከመቀበል ጀምሮ ሌሎች ለጉባኤው አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን በማድረግ ጉባኤውን የተሳካ ለማድረግ የአንድ ወገን ሥራ ብቻ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
 
ጉባኤው ዘላቂ አፍሪካዊ ወንድማማችነት የሚጠናከርበት፣ ኢትዮጵያ አሁን በአፍሪካ ኅብረት ያላት ተደማጭነትና መሪነት ይበልጥ የሚጠናከርበት እንዲሁም የኢትዮጵያ በጎ ገጽታ ይበልጥ ጎልቶ የሚወጣበት እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
 
ቱሪዝም ሚኒስቴር ለጉባኤው ስኬት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተደጋግፎ እንደሚሰራ ጠቁመው፥ እነዚህ አካላት ለጉባኤው ስኬታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ነው ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ የጠቆመው።
 
የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት ፥ ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ጉባኤው ከመካሔዱ በፊት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉ ችግሮችን ለማቃለል ይረዳል።
 
አዲስ አበባ የሚመጡ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን አስደስተን ለመሸኘት የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.