አጅባር ደብረታቦር
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጥር በተለያዩ የጎዳና ላይ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትእይንቶች የደመቀች መልከ ብዙ ወር ናት።
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በታህሳስ 29 በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ የልደት በአል ይጀምርና ጥምቀት እና ዘገሊላ በሰሜን ጎንደር፣ አመታዊ የታንኳ ፌስቲቫል ጣና ሃይቅ ላይ ባህር ዳር፣ የጊዮን በአል ሰከላ፣ አመታዊው የፈረስ ጉግስ በአል በእንጅባራ እያለ ቀጥሎ ወደ መገባደጃው ደግሞ ዛሬ በደቡብ ጎንደር ደብረታቦር ከተማ የአቡነ መርቆሪዮስ በአለ ንግስ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል።
በደብረ ታቦር አጅባር ሜዳ ላይ በየአመቱ ጥር 25 በደማቅ ሁኔታ የሚከበረው የአቡነ መርቆርዮስ በአለ ንግስ በክልሉ ጎብኚዎችን ሊስብ የሚችል አቅም አለው፡፡
በበአሉ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ጌታቸው ጀንበር፣ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹእ አቡነ ሚካኤል፣ የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ጣሂር መሀመድ፣ የፌደራል ቤቶች ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ጀንበር ተገኝተዋል።
በ1327 ዓ.ም እንደተመሰረተች የሚነገርላት ደብረ ታቦር ከተማ የአጼ ቴዎድሮስ መናገሻ እና በታሪክ የሚታወቀው የሴባስቶፖል መድፍ የተሰራበት ጋፋት እዚሁ የሚገኝባት ነው።
ዶ/ር ጌታቸው ፥ ” እድሜዋን የሚመጥን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲኖራት በርካታ ተግባራዊ ለውጦች ማድረግ ይጠበቅብናል ፤ ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ የመጡ እንግዶች መዋዕለ ነዋያቸውን በዚህች ታሪካዊ ከተማ እንዲያውሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን” ብለዋል።
በአሉ ከሃይማኖታዊ ስነስርአቱ ጎን ለጎን በበርካታ ባህላዊ ክንዋኔዎች ይደምቃል፡፡ አንዱ እና በርካቶች በጉጉት የሚጠብቁት ደግሞ የፈረስ ጉግስ ትእይንት ነው።
አመት ጠብቆ በሚደምቀው በዚህ የፈረስ ጉግስ ትእይንት ላይ ከከተማዋ የተለያዩ ዞኖች የተመረጡ ፈረሰኞች ይሳተፋሉ።
በከተማዋ የተዘረጉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ነገ በሚካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ከዳያስፖራዎች ጋር እንደሚመከር ከከተማው ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በመዓዛ መላኩ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!