Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለአገሬ የዋሉት ውለታ ሁሌም የሚታወስ ነው – የደቡብ ሱዳን የሽግግር ም/ቤት አፈጉባዔ

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለአገራቸው የዋሉት ውለታ ሁሌም የሚታወስ መሆኑን የደቡብ ሱዳን የሽግግር ም/ቤት አፈጉባዔ ጄማ ኑኑ ኩምባ ተናገሩ፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ከደቡብ ሱዳን የሽግግር ምክር ቤት አፈጉባዔ ጄማ ኑኑ ኩምባ ጋር ተወያይተዋል።

አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት፥ በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ሠላምና ፀጥታን በማስጠበቅ እንዲሁም በመሠረተ-ልማትና በድንበር ንግድ መተሣሠር አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የህዝብ-ለህዝብ ትብብርን ከማጠናከር ጋር በተያያዘም የፓርላማ -ለፓርላማ ግንኙነትን ማቀላጠፍ፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲን ማጠናከር፣ የምሁራንና የታዋቂ ግለሰቦች መድረኮችን መፍጠር፣ የጋራ ኮሚሽን ማጠናከር እና በፀጥታና ልማት ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ የተለያዩ የጋራ ኮሚቴዎችን ማቋቋም አስፈላጊነትን አንስተው መክረዋል።

በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ልምድ ለማጋራት እንዲቻልም የደቡብ ሱዳን አቻቸው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የፓርላሜንታዊ የሥራ ጉብኝት እንዲያካሂዱ ጋብዘዋል።

የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው ፥ በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ያልሆኑና የጎሣ ግጭቶች የፀጥታ ችግር እየፈጠሩ በመሆኑ የሁለቱ አገራት የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ በውይይት ላይ የተመሠረተ ዘለቄታዊ መፍትሔ ከመፈለግ አንፃር በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ዝግጁነት አስታውቀዋል።

አፈ-ጉባዔ ጄማ ኑኑ ኩምባ በበኩላቸው ፥ የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ረጅም የጋራ ታሪካዊ ዳራ ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው ፥ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለአገራቸው የዋሉት ውለታ ሁሌም የሚታወስ መሆኑን ተናግረዋል።

የድንበር አካባቢን ሠላም ማስጠበቅና ንግድን ማጠናከር እንዲሁም በመሠረተ-ልማቶች የመተሣሣር ጉዳዮችን በሚመለከት የጋራ ኮሚሽን በማቋቋም በትብብር ለመሥራት አፈ-ጉባዔዋና ፓርላማቸው ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እና የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት አገራትና ኢጋድ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ፍስሃ ሻውል እና በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ በውይይቱ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ልዑክ በጁባ ባደረገው ቆይታ የተሳካ ውይይቶችን እንዳካሄደ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.