Fana: At a Speed of Life!

ለሕብረቱ ጉባኤ 15 የግልና የመንግሥት ሆስፒታሎች በልዩ ዝግጅት አገልግሎት እየሰጡ ነው – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎችና ስራ አስፈጻሚዎች ጉባኤ 15 የግልና የመንግሥት ሆስፒታሎች በልዩ ሁኔታ ዝግጁ ሆነው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጤና ሚኒስቴር የአፍሪካ ሕብረት የሐኪሞች ቡድን አስተባባሪ ዶክተር ማራኪ መሐሪ ለኢዜአ እንደገለጹት ፥ የጤና ሚኒስቴር ለአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ለድንገተኛ አደጋ ህክምና ሰፊ ዝግጅት በማድረግ አገልግሎት እየሰጠ ነው።

ጉባኤው በሚካሄድበት በአፍሪካ ሕብረት ተቋም ውስጥ የተሳታፊዎችን ጤና ከመጠበቅ አንጻር 14 አባላት ያሉት የድንገተኛ የሕክምና ቡድን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም አንድ ልዩ አምቡላንስና ሁለት ሞባይል ክሊኒኮችን በመመደብ በስፔሻሊስት ሐኪሞችና ነርሶች አማካኝነት አገልግሎት እየተሰጠ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ከሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባበርም በ10 ደንኳኖች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

እስካሁን 9 ሺህ የሚጠጉ የኮቪድ-19 ምርመራዎች መከናወናቸውን ገልጸው ፥ ቫይረሱ የተገኙባቸውን በመለየት ህክምና የመስጠት ስራ እየተሰራ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

በዋናነት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ 11 የመንግሥት ሆስፒታሎችን ዝግጁ በማድረግና ባለሙያዎችን እስከ ጤና ጣቢያ ድረስ በመመደብ እየተሰራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለልዩ እንግዶች ከአራት የግል ሆስፒታሎች ጋር በመነጋገር ለድንገተኛና ለኮቪድ-19 ህክምና ልዩ ዝግጅት እንዲያደርጉ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በሕብረቱ ጉባኤ አገልግሎቱን የሚሰጡ ባለሙያዎች የጉባኤው ልዩ ልዩ ስብሰባዎች ተጀምረው እስከሚጠናቀቁበት እኩለ ሌሊት ድረስ በሙሉ ዝግጁነት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝም ነው ዶክተር ማራኪ የገለጹት።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.