የኢትዮ-ሱዳን የወዳጅነት የባህል ምሽት በካርቱም ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ-ሱዳን ወዳጅነት ማኅበር በሱዳን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የባህል ምሽት በካርቱም ተካሄደ፡፡
በዝግጅቱ ላይ በሱዳን የኢትዮጵያ ባለሙሉሥልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ አምባሳደርና የአፍሪካ አምባሳደሮች ቡድን ዲን አደራሂም አብዱላይ፣ በሱዳን የኤርትራ አምበሳደር ኢሳ አህመድ፣ የሱዳን ዓለም አቀፍ ሕዝቦች ወዳጅነት ምክር ቤት ዋና ፀሀፊ ሳልዋ መሀመድ፣ የኢትዮ-ሱዳን ወዳጅነት ማህበር አመራር አባላት እንዲሁም ኢትዮጵያውያን እና ሱዳናዊያን ተሳትፈዋል፡፡
አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት÷ የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ትስስር ዘርፈ ብዙና ታሪካዊ፣ የወደፊት እጣ ፋንታቸውም የተሳሰረ ነው ፡፡
የሱዳን እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተመሳሳይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የፖለቲካ ችግሮች ያሉባቸው ሕዝቦች በመሆናቸው÷ በመካከላቸው ያለውን መደጋገፍ በማጠናከር የጋራ ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ ለሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመው÷ የሁለቱን ሕዝቦች ሁለንተናዊ ትስስር ለማጎልበት የኢትዮጵያ ወገን ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል፡፡
የሱዳን ዓለም አቀፍ ሕዝቦች የወዳጅነት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሳልዋ መሃመድ በበኩላቸው÷የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ተመሳሳይ የቆዳ ቀለም፣ የጋራ ባህል እና የጋራ ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአንዱ አገር ዜጋ በሌላው በነፃነት የሚኖር፣ በአጠቃላይም በሰው ሠራሽ ድንበር የተለየ በሁለት አገር የሚኖር አንድ ህዝብ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነን ማለታቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!