በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በወራሪው እና አሸባሪው የህወሓት ቡድን ስር ለወራት በቆየው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የ2014 ምርት ዘመን የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ተጀመረ።
የአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን ÷ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በሽብር ቡድኑ ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰበት እና አሁንም የዞኑ የተወሰኑ ወረዳና ቀበሌዎች በሽብር ቡድኑ ስር መሆናቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ወራሪው ቡድን ከአብዛኛው የዞኑ ወረዳዎች በመወገዱ ወደቀደመ ኑሯቸው የተመለሱ የአካባቢው ነዋሪዎች የአፈር እና ውሃ እቀባ፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራን ጀምረዋል ብለዋል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሀይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው÷ ዞኑ በሽብር ቡድኑ ከደረሰበት ውድመት እንዲያገግም ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁመው÷ በዚህም በክልሉ 472 ሺህ ሄክታር መሬትና 8 ሺህ 429 ተፋሰስ በዘንድሮው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ እንደሚለሙ አንስተዋል።
በዞኑ የግብርና ልማት ስራ በሽብር ቡድኑ ምክንያት ዘግይቶ ቢጀመርም÷ ማህበረሰቡ ከደረሰበት ወረራ ተላቆ የስነ-ምህዳር ጥበቃ ስራውን መጀመሩ በቀጣይ ዓመት ለሚኖረው ምርትና ምርታማነት እና ዘላቂ ልማትን ለማስቀጠል ጠቀሜታው ከፍያለ ነው ብለዋል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታው ጌታሁን በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት÷ በዞኑ 40 ሺህ ሄክታር መሬት እና 80 ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራወቹ የሚሰሩ ሲሆን÷ ስራው እስኪጠናቀቅ 97 ሺህ የህብረተሰብ ክፍል ይሳተፋል ብለዋል፡፡
የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው ለ 15 ቀናት በንቅናቄ የሚቀጥል ሲሆን÷ ስራው ግን በቋሚነት ዓመቱን ሙሉ እንደሚከወን ገልጸዋል፡፡
በኤልያስ አንሙት
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!