Fana: At a Speed of Life!

በህገ-ወጥ መንገድ በተሽከርካሪ ተጭኖ ሲጓጓዝ የነበረ ከ9 ሺህ በላይ ጥይት መያዙን ፖሊስ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህገ-ወጥ መንገድ በተሽከርካሪ ተጭኖ ሲጓጓዝ የነበረ ከ9 ሺህ በላይ ጥይት የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር ባደረጉት ክትትል በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ እንደገለጸው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B27307 አ/አ የሆነ ፒካፕ ተሽከርካሪ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በማዘዋወር ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው የካቲት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ነው፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ እንደገለፀው÷ ተሽከርካሪው መነሻውን ደብረ ብርሃን ከተማ በማድረግ 8 ሺህ 465 የክላሽን-ኮቭ እና 661 የብሬን ጥይት በካልሲዎች በመጠቅለል በተሽከርካሪው የጭነት መጫኛ ላይ በተሸፈነ ማይካ ውስጥ ደብቀዉ ሲጓኋዙ ነበር የተያዘው።
የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመተባበር ባደረገው ክትትል ከምሽቱ 4 ሰዓት ገደማ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ጎሮ ሰፈራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲደርስ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
አሽከርካሪው ህገ-ወጥ ጥይቱን ለመጫን 2 ሺህ 500 ብር ሊከፈለው እንደተስማማ የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ ግለሰቡ በተጠረጠረበት ወንጀል በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት ይገኛል ብሏል፡፡
ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ እና ያስገኘው ውጤት ከፍተኛ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በእስካሁኑ ሂደትም ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት በርካታ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር በማዋል በህግ እንዲጠየቁ እያደረገ እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተመሳሳይ ከወልዲያ ተነስቶ ወደ ባህርዳር በኮድ 3 አማ የታርጋ ቁጥር 23128 በሆነ ተሽከርካሪ ሲጓዝ የነበረ በርካታ የክላሽ ተተኳሽ ጥይት ከሁለት ተጠርጣሪወች ጋር እጅ ከፍንጅ መያዙን የደብረ ታቦር ከተማ 1ኛ ፖሊስ ጣቢያ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
የጽ/ቤቱ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ሀይሌ መለሰ እንደገለጹት÷ በዛሬው ዕለት ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ በተጠቀሰው ተሽከርካሪ ተጭኖ ሊያልፍ የነበረ 7 ሺህ 228 የክላሽ ተተኳሽ ጥይት ከሁለት ተጠርጣሪወች ጋር እጅ ከፍንጅ ሊያዙ ችለዋል፡፡
ተመሳሳይ ወንጀሎችን ለመከላከል እና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን ለማስቆም ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካሉ ጋር በቅንጅት እየሰራ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ዋና ኢንስፔክተር ሀይሌ ጥሪ ማቅረባቸውን ከደብረ ታቦር ከተማ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.