Fana: At a Speed of Life!

ለ2ኛው ዙር የኮቪድ- 19 ክትባት ዘመቻ መሳካት መገናኛ ብዙኃንና አመራሮች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከየካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በዘመቻ መልክ ለሚሰጠው የኮቪድ- 19 ክትባት የመላው ህብረተሰብ ተሳትፎ እንዲጠናከር የመገናኛ ብዙኃን እና በየደረጃው ያሉ አመራሮች አስፈላጊውን ቅስቀሳና ድጋፍ እንዲያደርጉ የጤና ሚኒስቴር ጠየቀ።
በሚኒስቴሩ የእናቶችና ህፃናት ጤና ረዳት ዳይሬክተር እና የክትባት አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ላቀው እንደገለፁት፥ የኮቪድ -19 ወረርሽኝ አሁንም የጤና ስጋት በመሆኑና ዜጎች እየሞቱ ስለሆነ ዘመቻውን ማድረግ አስፈልጓል።
ለክትባት የሚሆን ከ20 ሚሊየን በላይ ዶዝ ለሁሉም ክልሎች መላኩንና ባለሙያዎችም ሰልጥነው መሰማራታቸውን የገለፁት አቶ ዮሐንስ፥ ህብረተሰቡ በክትባቱ በሚገባ ተሳተፎ ራሱንና ቤተሰቡን በማስከተብ ቫይረሱ ከሚያስከትለው ስቃይና ሞት እንዲከላከል የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ቅስቀሳ በማድረግና ግንዛቤ በመፍጠር አመራሮች ክትትልና ድጋፍ በማድረግ እንዲረባረቡ ጠይቀዋል።
ባለፈው ህዳር ወር ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ዘመቻ 10 ሚሊየን ሰዎችን በክትባቱ መድረስና ከበሽታው መታደግ መቻሉን ገልጸው፥ ሁለተኛውን ዙር የክትባት ዘመቻም ለማሳካት ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዮርዳኖስ አለባቸው በበኩላቸው፥ ኮቪድ -19ን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል የተሰራው የተቀናጀና የተደራጀ ስራ ውጤትማ እንደነበር ጠቁመው፥ በቀጣይም ህብረተሰቡ በሽታውን አቅልሎ እንዳያይና ከመዘናጋት እንዲወጣ መገናኛ ብዙኃን ወረርሽኙ የሚያደርሰውን ጉዳት በተለያዩ አቀራረቦች በተከታታይ እንዲሰሩ መጠየቃቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የደቡብ ክልልም በዚህ ዘመቻ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የኮቪድ -19 መከላከያ ክትባት መዘጋጀቱን የክልሉ ርዕሠ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ አስታውቀዋል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መልኩን እየቀያየረ መምጣቱ አሳሳቢ በመሆኑ ይህንን በሽታ ለመከላከል በክልሉ የሞት እና የበሽታው ምጣኔ እንዳይጨምር ክትባቱ ምንም አይነት ችግር የሌለው መሆኑን በመረዳት ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት ጀምሮ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች 2ኛውን ዙር ክትባት እንዲከተቡ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.