በሩሲያ-ዩክሬን ውጥረት ምክንያት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል በተፈጠረው ውጥረት ሳቢያ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ለሰባት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ማሻቀቡ ተገልጿል፡፡
ውጥረቱን ተከትሎ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች አሜሪካ እና አውሮፓ በዓለም የነዳጅ ምርት ላይ እገዳ ሊያደርጉ ይችላሉ በሚል ስጋት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡ እየተነገረ ነው፡፡
በዚህም በዛሬው ዕለት የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋ በ 1 ነጥብ 4 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ተመላክቷል፡፡
የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከዩክሬን ሩሲያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት እንዳለው እና ሁኔታውን የሚመጥን ማሻሻያዎች እንደሚጠበቁ ነው የተገለጸው፡፡
በሌላ በኩል በዘርፉ ኢንቨስት የሚያደረጉ ባለሃብቶች በአሜሪካና ኢራን መካከል በ2015 የተደረገውን የኒውክሌር ስምምነት ለማደስ እያደረጉት ያለውን ውይይት በአንክሮ እየተከታተሉት ያለ ሌላ ወሳኝ ጉዳይ ነው ተብሏል፡፡
ይሁን እንጂ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ውጥረት ከማሻሻል ይልቅ ይበልጥ እየተባባሰ እንደመጣ አንድ የኢራን ደህንነት ባለስልጣን መናገራቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡